ቀጥታ፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ይሰራል

ጂንካ፤ የካቲት 1/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የክልሉ መንግሥት ገለጸ።

የፃማኮ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ የባርባይሳ በዓል በደቡብ ኦሞ ዞን በናፀማይ ወረዳ ብራይሌ ቀበሌ በድምቀት ተከብሯል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት ይሰራል።

የክልሉ መንግሥት ለብዝሃ ባህል፣ ቋንቋና እምነት እውቅና እየሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።

የክልሉ ሕዝቦች ሕገ መንግስቱ በሰጣቸው ዕውቅናም ተጠቅመው ባህላቸውን የማልማት፣ የማስተዋወቅና ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ ዕድል እንዳላቸውም ተወካዩ ገልጸዋል።

የፃማኮ ብሔረሰብ እንደ ባርባይሳ ያሉ ጠቃሚ ባህልና እሴት ያሉት ቢሆንም፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ትኩረት ሳያገኝ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን መንግሥት በሰጠው ትኩረት ባህሉ እያደገና ዕውቅና እያገኘ መጥቷል ብለዋል አቶ ንጋቱ።

የክልሉ ብሔረሰቦች ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ ድጋፍ እንደሚደረግም ተወካዩ አረጋግጠዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማዕከል ማልኮ በበኩላቸው በዞኑ የሚከበሩ ባርባይሳን የመሰሉ ባህላዊ ክብረ በዓላት ወንድማማችነትና እህትማማችነትን እያጠናከሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

''የደቡብ ኦሞ ዞን በርካታ ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚኖሩባት ትንሿ ኢትዮጵያ ናት" ያሉት አቶ ማዕከል፤ ''ይህም ብዝሃ ባህል ለአብሮነት መጠናከርና የጋራ እሴት ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው'' ነው ያሉት።

በቀጣይም የጋራ እሴቶችን ለማጉላትና አብሮነት ለማጠናከር በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ባርባይሳ ቂምና ቁርሾን አስወግዶ ዕርቀ ሰላም የማስፈን አቅም ያለው ክብረ በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የበናፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ጋያ ናቸው።

"የባርባይሳ በዓል በውስጡ ጠቃሚ እሴቶች ያሉት በመሆኑ ከዞንና ከወረዳ አልፎ የዓለም ቅርስ እንዲሆን ያልተቆጠበ ድጋፍ ይደረጋል" ብለዋል።

ከፃማኮ ብሔረሰብ  የበዓሉ ታዳሚ አቶ ጋልቦ ጉሜ  በዓሉ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አኩሪ ባህል መሆኑን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት በሰጠው ትኩረት በዓሉ በአደባባይ በይፋ መከበር መጀመሩን ገልጸው፣ በቀጣይም በዓሉ በይበልጥ እንዲተዋወቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ''ባርባይሳ ለሰላም፣ ለልማትና ለብልፅግና!" በሚል መሪ ሀሳብ በተከበረው በዓል ላይ ከአጎራባች ዞንና ወረዳዎች የመጡ ተሳታፊዎችም ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም