የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለመንግስት ልማት ድርጅቶች የሽግግር መርሐ ግብር አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ለመንግስት ልማት ድርጅቶች የሽግግር መርሐ ግብር አዘጋጀ
አዲስ አበባ ፤የካቲት 01/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ውጤታማ አፈጻጸም የሚያሸጋግር መርሐ ግብር ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሥሩ ካሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጋር የ2016 ዓ ም ስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማካሄድ ጀምሯል።
ከዛሬ የካቲት 1 እስከ 12 /2016 ዓ.ም ድረስ በሚቆየው ግምገማ፥ የልማት ድርጅቶች በግማሽ ዓመቱ ያከናወኗቸው ተግባራት፣ ያሉ ችግሮች እና የመፍትሔ እርምጃዎች በዝርዝር ውይይት ይደረግባቸዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሃብረቢ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውጤታማ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የድጋፍ ማዕቀፎች እየተዘረጉ ነው።
በዚህም አብዛኞቹ ድርጅቶች ከኪሳራ ወጥተው ወደ ውጤታማነት መሸጋገራቸውንም ነው ያነሱት ምክትል ሥራ አስፈጻሚዋ።
አሁንም ከኪሳራ ያልወጡ ጥቂት ድርጅቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ እነዚህ ድርጅቶች ወደ አትራፊነት እንዲሸጋገሩና ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ የሚያስችል የሽግግር መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን ቦርድ መጽደቁን ጠቁመው፥ ኪሳራ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ድርጅቶች አትራፊ የሚሆኑበትን ዝርዝር እቅድ የያዘ መሆኑንም አብራርተዋል።
እንደ ወይዘሮ ያስሚን ገለጻ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የበለጠ ስኬታማ እንዲሆኑ ጠንካራ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓት የተዘረጋ ሲሆን በዚህም አበረታች ውጤት እየተገኘ ነው።
በተለይም የበለጠ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች በትኩረት በማጤን የአገሪቷን ኢኮኖሚ የሚያነቃቁ አሰራሮች ገቢራዊ ተደርገዋል ብለዋል።
ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት፤በዛሬው ዕለት የተጀመረው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም ግምገማ ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሥሩ የሚገኙ 27 የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ይታወቃል።