ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የእዳ ጫናን ለመቀነስ የያዘችው ውጥን እንዲሳካ የአገር ውስጥ ምርትና የወጪ ንግድን በማስፋት ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል- የምጣኔ ሃብት ምሁራን

አዲስ አበባ ፤የካቲት 01/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የእዳ ጫናን ለመቀነስ የያዘችው ውጥን እንዲሳካ የአገር ውስጥ ምርትና የወጪ ንግድን በማስፋት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መንግስት በብድር በሚያስፋፋው መሠረተ ልማት ላይ የተንጠለጠለ ሆኖ መቆየቱ የዋጋ ግሽበትና የብድር ጫና እንዲፈጠር ማድረጉ ይገለጻል።

የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከተወሰኑ የግብርና ምርቶች አቅርቦት ተላቅቆ አስተማማኝ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት ተስኖት መቆየቱም የብድር ጫናውን አባብሶታል።

ይህን መነሻ በማድረግ በአስር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ከ2013-2022 ዓ.ም ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቶታል።

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ የዕዳ ጫና ለማቃለልና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። 

የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ካስመዘገባቸው ትላልቅ ስኬቶች ዋነኛው ዕዳ ቅነሳ ላይ የያዘው አቋም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ወለድ ያለው የንግድ ብድር ትበደር እንደነበር አስታውሰው ከለውጡ በፊት የውጭ ዕዳ ከሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ ድርሻ ነበረው ብለዋል።

ነገር ግን ባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት ምንም አይነት የንግድ ብድር አለመበደሩን ጠቅሰው 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ መክፈል መቻሉን አንስተዋል።

በዚህም የአገሪቱን የውጭ ዕዳ ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉንና በቀጣይ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ምሁራን ኢትዮጵያ ዕዳ የመክፈል አቅሟን የበለጠ ለማሳደግ የአገር ውስጥ ምርትና የወጪ ንግድን ማስፋት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባት ተናግረዋል።

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር ሞላ አለማየሁ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ከተለያዩ አገራት የተበደረችውን ብድር በተለያዩ መንገዶች እየከፈለች መሆኑን አንስተዋል።

ነገር ግን ዕዳ የመክፈል አቅሟ የበለጠ እየጎለበተ እንዲመጣ የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግና የውጭ ምንዛሬን መቆጠብ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት እንደመሆኗ በተለይም የምግብ ፍጆታን በአገር ውስጥ በማሟላትና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመቀነስ ለዚህ የሚወጣውን ገንዘብ ዕዳ ወደ መክፈል ማዞር እንደሚገባት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ወደ ውጪ የምትልካቸውን ምርቶች በብዛትና በጥራት በመጨመር ከወጪ ንግዱ የሚገኘውን ምንዛሬ የዕዳ ክፍያን ጨምሮ ለተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ማዋል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶክተር አቡሌ መሃሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያለባትን ዕዳ ለመቀነስም ሆነ የዕዳ ሽግሽግ ለማድረግ በቂ የውጭ ምንዛሬ ሊኖራት እንደሚገባ አንስተዋል።

የውጭ ምንዛሬ ገቢውን ለማሳደግ ደግሞ አገሪቷ ከውጭ የምታስገባቸውን ምርቶች መቀነስና የገቢ ምንጮቿን ማስፋት እንዳለባት ነው የገለጹት።

በ10 ዓመት የልማት ዕቅዱ የውጭ ምንዛሬን እንዲያስገኙ ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች መለየታቸውን የገለጹት ዶክተር አቡሌ በተለይም የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የገቢ ምርቶችን ለመተካትና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያላትን ውስን ሃብት በመጠቀም የውጭ ዕዳዋን ለመክፈል ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ወጪ ምርቶችን የሚያሳድጉ እንዲሁም የዋጋ ግሽበቱን መቀነስ የሚችሉ ዘርፎች ላይ የበለጠ ማተኮር እንዳለባት ተናግረዋል።

በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች እየተስተዋለ ያለው የጸጥታ ችግር የሚፈለገውን ያህል ምርት እንዳይመረትና ወደ ውጭ ገበያ እንዳይቀርብ እንቅፋት መሆኑን ያነሱት ምሁራኑ ይህንን በመሰረታዊነት መለወጥና ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም