ቀጥታ፡

 የአልነጃሺ መስጊድ የሚገኝበት ስፍራን በማልማት የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትብብር መስራት ያስፈልጋል-ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ

መቀሌ፤የካቲት 01/2016 ፡-የአልነጃሺ መስጊድ የሚገኝበት ስፍራን በማልማት የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በአልነጃሺ መስጊድ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት፤ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ስፍራዎች አንዱ የአልነጃሺ መስጊድ ነው። 

''ባህላችንን እና ታሪካችንን ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን'' ያሉት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰበት የአልነጃሺ መስጊድ  የተቋረጠውን ጥገናና የማስፋፊያ የልማት ፕሮጀክት መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

የአልነጃሺን ታሪካዊ ስፍራ በመንከባከብና በማልማት ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። 


 

የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ኡዝታዝ አቡበከር አሕመድ በበኩላቸው ፣ከኢትዮጵያ አልፎ ለዓለም ማህበረሰብ ትልቅ የታሪክ አሻራ ያለው የአልነጃሺ መስጊድ ስፍራን ማልማት የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።      


 

ሥፍራውን አልምቶ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የፌደራል መንግስት ድጋፍና ትብብር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼክ አደም ዓብዱልቃድር ናቸው።   

  የአልነጃሺ መልሶ ግንባታ የልማት ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስዒድ መሐመድ ብርሀን በበኩላቸው፣ የአልነጃሺ መስጊድ የሚገኝበት ሥፍራ ለክልሉ ብሎም ለኢትዮጵያ አልፎ ተርፎም ለዓለም ትልቁ ሃብት ነው። 

የልማት ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል እና ስፍራውን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

 የአልነጃሺ መስጊድ የጥገና ስራ ለማከናወን እና የማስፋፊያ የልማት ፕሮጀክትን ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም የትግራይ ክልል ባህል ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በጋራ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም