ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ለትምህርት ጥራት መሰረት የሚጥሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ዶክተር ቶላ በሪሶ  

አዲስ አበባ፤ የካቲት  01/2016 (ኢዜአ)፦  በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤት ምገባን ጨምሮ ለትምህርት ጥራት መሰረት የሚጥሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ገለጹ፡፡ 

በኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አዘጋጅነት የሚካሄደው" መሪ በልበሎሚ " የተሰኘ የውይይት መድረክ በክልሉ የትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ትኩረቱን በማድረግ ተካሂዷል፡፡  

በሀገር ደረጃ አዲስ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተነድፎ በሁሉም ክልሎች ትግባራዊ በመደረግ ላይ  ሲሆን፤ ማሻሻያው ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ሙያዊ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ ይታወቃል፡፡   

በኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አዘጋጅነት በሚካሄደው "መሪ በልበሎሚ" የተሰኘ የውይይት መድረክ ላይ የተሳተፉት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኋላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ፤ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የነበረውን ስብራት ለመጠገን በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በኦሮሚያ ክልልም የተማሪዎችን ምገባ ስርዓት የማስፋፋት፣ የመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ቤቶችን የመገንባት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎችን ጨምሮ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ 

ለአብነትም በክልሉ እስካሁን ባለው ሂደት 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው በመጪው ጊዜያት ይህን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡  

በሌላ መልኩም ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ የማድረግ እና ግብዓቶችን የማሟላት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

የትምህርት ቤቶችን በማሻሻሉ ሰራ ላይ ህብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ ማድረጉንም እንዲሁ፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት 34 ሺህ በላይ ተጨማሪ መማሪያ ክፍሎች በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በክልሉ የመዋዕለ ህጻናት ተደራሽነትን ከማስፋት አንጻር በህዝብ ተሳትፎ 14 ሺህ 700 የሚሆኑ መዋዕለ ህጻናት መገንባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ጉዳይ የሁሉም አካላትን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ጠቅሰው ከዚህ አኳያ መምህራን፣ ወላጆች፣ አንዲሁም በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተሳትፎአቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል፡፡

የአዲሱን ስርዓተ ትምህርት መጽሐፎች ተደራሽ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደትም 15 ሚሊዮን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም  6 ሚሊዮን የሁለተኛ ደረጃ መጻሕፍት ወደ ትምህርት ቤቶች መሰራጨታቸውን  ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም መጽሐፎችን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ የማድረግ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም