ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በጋራ የመልማት ዲፕሎማሲያዊ መርህን የተከተለና የቀጣናው ሀገራትን ትብብር የሚያሳድግ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት  01/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት በጋራ የመልማት ዲፕሎማሲያዊ መርህን የተከተለና የቀጣናው ሀገራትን ትብብር የሚያሳድግ መሆኑ የህግና  ምጣኔ ሃብት ምሁራን ገለጹ ።

ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሰሞኑ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ሀገር ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ በሰጥቶ በመቀበል መርሕ እየሰራች መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ ከህዝብ ቁጥርና እያስመዘገበች ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አንጻር የባህር በር እንደሚያስፈልጋት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም ይህንን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ የትኛውንም ሀገር የሚጎዳ ሳይሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ በጋራ መልማትን የሚያጎለብት መሆኑንም አጽዕኖት ሰጥተው መናገራቸው ይታወቃል።

በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምሕር የሆኑት ዶክተር ማናየ ዘገየ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ ነው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1982 ባወጣው ዓለም አቀፍ የባሕር በር ሕግ መሰረትም ወደብ የሌላቸው ሀገራት  በአካባቢያቸው ባሉ ባሕሮች መጠቀም እንደሚችሉ ይደነግጋል ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ ሰጥቶ የመቀበል መርሕን ጨምሮ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገው ጥረት ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሕግ መከበር መስዋእትነት ስትከፍል የኖረች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤  ከጎረቤቶቿም ሆነ ከሌላው አጋራት ጋር ሕግን አክብራ እንደምትሰራም ነው ያነሱት።

የባሕር በር ጉዳይ በዲፕሎማሲ፣በውይይትና በድርድር የሚፈታ ነው የሚሉት ዶክተር ማናየ፤ የኢትዮጵያ ጥያቄ ከራሷ አልፎ የአካባቢው ሀገራትን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ትስስር የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚ መምሕርና ተመራማሪ ዶክተር ዱጋሳ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገትና የመልማት ፍላጎት አንፃር የባህር በር እንደሚያስፈልጋት አብራርተዋል፡፡

ይሕም ሕዝቦቿን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ትስስርን ይበልጥ የሚያሳድገው እንደሆነ አንስተዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየሄደችበት ያለውን አካሄድ አጠናክራ መቀጠል እንደሚጠበቅባት ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ቁጥር መጨመርና የኢኮኖሚ እድገት አንፃርም የባሕር በር ጥያቄዋ የዘገየ መሆኑንም የኢኮኖሚ ምሁሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ለምታገኝው የወደብ አገልግሎት በዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም