አዲስ አበባን ወደ ስማርት ሲቲ መቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን ወደ ስማርት ሲቲ መቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2016(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባን ወደ ስማርት ሲቲ መቀየር የሚያስችል የቴክኖሎጂና መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራዎች እየተፋጠነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አስታወቀ ።
በከተሞች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት አለመዘርጋቱ፣ በፕላን እንዲመሩ ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውና በዕድገታቸው ዙሪያ ወጥ-ግንዛቤ አለመኖር በዜጎች ላይ የመልካም አስተዳደር ችግር እየተፈጠረ ይገኛል።
ችግሩን ለመቅረፍ ከተሞች በፕላን እንዲመሩና ዜጎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የ”ስማርት ሲቲ” አሠራርን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ይታወቃል።
በኢትዮጵያም ከተሞችን ስማርት ሲቲ ለማድረግ ሰፊ አንቅስቃሴ እየተካሄደ መሆኑም ይታወቃል።
ኢዜአ አዲስ አበባን ስማርት ሲቲ ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮን አነጋግሯል።
የቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የስማርት ሲቲ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቱሉ ጥላሁን መዲናዋ በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚስተናግዱባት ከተማ ናት ሲሉ ይገልፃሉ።
በተጨማሪም በርካታ ዜጎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት በስፋት ወደ መንግስት ተቋማት እንደሚሄዱም ይስተዋላል።
ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳለጡና ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ እና ዘመናዊ አገልግሎት ለመስጠት በርካታ ተግባራትን እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህም ለዜጎች የዘመነ አገልግሎትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችውን አዲስ አበባ ወደ ስማርት ሲቲ ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።
ቢሮውም የተጀመረው መዲናዋን ወደ ስማርት ሲቲ የመቀየር ተግባር ስድስት አንኳር ጉዳዮችን በመለየት ቴክኖሎጂዎችን የማልማት እና መሰረተ ልማትን ምቹ ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራት በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ለአብነትም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን የሚያሳልጡ፣ የአካባቢን ስነ-ምህዳር የሚያስውቡ ፣የመንግስት ተቋማትን አሰራር ማዘመን እና ቱሪዝምን ማልማት የሚያስችሉ ክንውኖች ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በቱሪዝም፣ በትራንስፖርት አገልግሎት እና ደኅንነት ዘርፎች ላይ የሚገኙ ተቋማቶች አገልግሎታቸውን ለማዘመን የሚያስችላቸው ቴክኖሎጂ እና መሰረተ ልማትን የማልማት ስራ እንደዚሁ እየተሰራባቸው እንደሚገኝ አክለዋል።
በተመሳሳይ ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲነት መቀየር ብቻ ከተማዋን ለማሳደግ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ፤ የለሙ ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም ማኅበረሰብ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በመሰራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ዶክተር ቱሉ ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲነት ለመቀየር ከተቋማት ጋር በቅርርብ መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በከተማዋ የሚገኙ ክፍለ ከተሞች እና ወረዳዎች እርስ በእርስ ቀልጣፋ በሆነ ኔት ወርክ የሚገናኙበትን ስራ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰራ መሆንን ገልጸዋል።
ቢሮው ከተማ አስተዳደሩ ሪፎርም ባደረገባቸው 16 ተቋማት አሰራርን ለማዘመን የሚያስችሉ 42 ቴክኖሎጂዎችን እና መሰረተ ልማቶች በማልማት በካቢኔ እንዲጸድቅ ማቅረቡን ተናግረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር የአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት አካል የሆነ የመሰረተ ልማት ግንባታ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት በ11 ክፍለ ከተሞች፣ በ120 ወረዳዎች፣ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ 44 ቢሮዎችን እንዲሁም የዋና ዳታ ማዕከሉን አሁን ከሚገኝበት በሜጋ ባይት የሚለካ የግንኙነት ፍጥነት በማሻሻል ከ1 ጊጋ ባይት እስከ 100 ጊጋ ባይት በሚደርስ እጅግ ከፍተኛ ፍጥነት እና ጥራት ባለው የኦፕቲካል ፋይበር ግንኙነት (Lamda Connectivity) በማስተሳሰር ለከተማ አስተዳደሩ እንደሚያስረክብ መዘገቡ ይታወሳል።