ቀጥታ፡

በነዳጅ ዋጋ ማሻሻያና የድጎማ ሥርዓት ሪፎርም 268 ቢሊየን ብር ሊደርስ የነበረውን ዕዳ ወደ 114 ቢሊየን ብር ዝቅ ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ የካቲት  01/2016 (ኢዜአ)፦  በነዳጅ ዋጋ ማሻሻያና የድጎማ ሥርዓት ሪፎርም 268 ቢሊየን ብር ሊደርስ የነበረውን ዕዳ ወደ 114 ቢሊየን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ገለጸ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የፊሲካል ፖሊሲ ስብራትን ለመጠገን ሪፎርም ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የልማት ድርጅቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ለአብነትም በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያና የድጎማ ሥርዓት ድርጅቱ በ2014 ዓ.ም የነበረበትን ዕዳ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተናግረዋል።  

በዘርፉ የተደረገውን ሪፎርም አጠናክሮ በማስቀጠል በአምስት ዓመታት ውስጥ ዕዳውን ዜሮ በማድረስ በቀጣይ የፊሲካል ፖሊሲ ስብራትን ይጠግናል ነው ያሉት። 


 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ እስመለዓለም ምህረቱ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የድርጅቱን ሪፎርም ለማከናወን አምስት መሰረታዊ ማስተካከያዎች ተደርገዋል።

የነዳጅ ዋጋ ማረጋጊያ ሥርዓቱን ማሻሻል፣ የታለመለት የነዳጅ ድጎማን በተወሰነ ጊዜ ገደብ ማስቀረት፣ ግብይቱን በቴክኖሎጂ ማዘመን፤ የግብይትና መሰረተ ልማት ችግሮችን መፍታት እንዲሁም ጠንካራ አስፈፃሚ አካላትን መገንባት መሆኑን አስረድተዋል። 

በዚህም በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም የነበረውን 181 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ዕዳ በአሁኑ ወቅት ወደ 114 ቢሊየን ብር ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

መንግሥት በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ሪፎርም ባያደርግ ኖሮ የድርጅቱ ዕዳ 268 ቢሊየን ብር ይደርስ እንደነበር አስረድተዋል። 

በሪፎርም በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ዕዳውን ዜሮ ለማድረስ እየሰራን ነው ያሉት አቶ እስመለዓለም፤ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ማሻሻያና የድጎማ ሥርዓት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

መንግሥት የድጎማ ሥርዓቱን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ስድስት ጊዜ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ለታለመለት ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች በቀን ያወጣው የነበረውን ወደ 90 ሚሊየን ብር አሁን ወደ 14 ሚሊየን ብር ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል። 

ነዳጅ የሚገባው በአገሪቱ አቅም ልክ ሳይሆን በፍላጎት ልክ መሆኑን የገለጹት አቶ እስመለዓለም፤ ኢኮኖሚው እያደገ በመምጣቱ የነዳጅ ፍላጎቱም እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

ለአብነት በ2015 በጀት ዓመት ለነዳጅ ግዥ የወጣው ወደ 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ከኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ጋር ተቀራራቢ መሆኑን በማሳያነት አንስተዋል። 

በዚህም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሚያስገባውን የነዳጅ ፍላጎት መጠን በየዓመቱ 10 በመቶ እየጨመረ እቅድ እንደሚይዝ ገልጸዋል።

ለአብነት በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወር 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ግዥ ተፈዕሞ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ሽያጭ ተከናውኗል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም