ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካዊያን ኩራትና የድል ተምሳሌት ነው- አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ የካቲት  1/ 2016 (ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካዊያን ኩራትና የድል ተምሳሌት መሆኑን በተለያዩ ሀገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ገለጹ።

የአድዋን ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ትልቅነትና የታሪክ ባለቤትነት በሚመጥን መልኩ ተገንብቶ በቅርቡ እንደሚመረቅ ይታወቃል።

ፕሮጀክቱን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት በሰጡት ማብራሪያ ፤የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያን ታላቅነት በሚመጥን መልኩ መገንባቱን አብራርተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ መደመር በተግባር የታየበት፣የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባና አመራሮች የእለት ተእለት ክትትል ያልተለየው የበርካቶች የትጋት ስራ ውጤት መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝብ ኩራት መሆን እንደቻለች አንስተዋል።

ዛሬ ላይ የአድዋ ድል ደማቅ ታሪክ ለትውልድ በምናብ ብቻ የሚነገር ሳይሆን አካል ለብሶ በዘመን መካከል እንዲነገርና እንዲታይ የሚያስችል ስራ በፕሮጀክቱ መካተቱን ነው የተናገሩት፡፡

የህንጻ ስነ-ጥበብ እና የግንባታ ጥራት፣ በውስጡ የያዛቸው የሁሉም ጀግኖች ታሪክና ምስል ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን ኩራት ከመሆን አልፎ ለመላው አፍሪካዊያን ኩራት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መነቃቃት የራሱን ድርሻ ይወጣል ነው ያሉት።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች ድምጽ በመሆን ጭቆናን እንድትታገል ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአድዋ ጀግኖች አንድነታቸውን ጠብቀው አገራቸውን ከወረራና ጫና መመከታቸውንም ነው ያስታወሱት፡፡

በመሆኑም የአድዋ ድል መታሰቢያ አሁን ያለው ትውልድ ለኢትዮጵያ ከፍታ የራሱን አሻራ ለማኖር እንዲተጋ ያስችለዋል ብለዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ለድል ጀግኖች መታሰቢያ ታልሞ የተገነባ ሲሆን፤ በውስጡም ሙዚየም፣ ምክር ቤት ፣የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ አምፊ ቲያትር፣ ቤተ መጻህፍት፣ የስነ ጥበብ ጋላሪዎች፣  የኢግዚቢሽን ማዕከላትና ሌሎችንም አገልግሎቶች ያካተተ እጅግ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም