በእብድ ውሻ በሽታ የሚከሰት ሞትን ወደ ዜሮ ለማውረድ እየተሰራ ነው -- የኢትዮጵያ ህብረተሰበ ጤና ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በእብድ ውሻ በሽታ የሚከሰት ሞትን ወደ ዜሮ ለማውረድ እየተሰራ ነው -- የኢትዮጵያ ህብረተሰበ ጤና ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታ ህክምና ተደራሽነትን በማስፋት በ2030 በበሽታው የሚከሰት ሞትን ወደ ዜሮ ለማውረድ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ባለፉት ስድስት ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ118 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ውሾች ክትባት መሰጠቱን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የባክቴሪያል፣ ፓራሳይቲክና እንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ቡድን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ይመር ሙሉጌታ፤ የእብድ ውሻ በሽታ(ሬቢስ) በቫይረሰ አማካኝነት የሚመጣና በአብዛኛው የሰውን የአንጎል ክፍል የሚጎዳ በሽታ ሲሆን የሚተላለፈውም በውሻ ንክሻ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሽታው እንደትኩሳት፣ውሃ መፍራት፣ መንቀጥቀጥና ቅዠት የመሰሉ የኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች እንደሚያሳይም አስረድተዋል።
ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው ምልክት ማሳየት ከጀመሩ በኋላ ታክሞ መዳን አዳጋች በመሆኑ ምልክት ከማሳየታቸው በፊት በአፋጣኝ ህክምና መስጠትና ቅድመ መከላከል ላይ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የህክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ለአብነትም በኢንስቲትዩቱ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን ህክምና ወደ ጤና ጣቢያዎች ማስፋት መቻሉን አውስተዋል፡፡
በዚህም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2030 በኢትዮጵያ በበሽታው ሳቢያ የሚከሰትን ሞት ወደ ዜሮ ለማድረሰ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት እና ቬተርነሪ ፐብሊክ ጤና መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ በበኩላቸው በበሽታው የሚደርሰውን የሞት መጠን ለመቀነስ ለውሾች ክትባት መስጠትና ህብረተሰቡ በየጊዜው ውሾችን እንዲያስከትብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በሀገሪቱ ካሉ ውሾቸ 70 በመቶ ያህሉን መከተብ ከተቻለ በበሽታው የሚደርሰውን ሞት ወደዜሮ ለማድረሰ ይረዳል ያሉት ዶክተር ውብሸት ባለቤት አልባ ውሾች የማምከን ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ118 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ውሾች ክትባት መሰጡንም ተናግረዋል፡፡
የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር (ሲዲሲ) ሪፖርት አንደሚያሳየው በኢትዮጵያ በዓመት በአማካኝ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ዜጎች በእብድ ውሻ በሽታ ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡