ቀጥታ፡

የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያው ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ሙያዊ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ሙያዊ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የትምህርት ሥርዓቱን ማሻሻያና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚኖረውን ፋይዳ በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ተማሪዎች ከንድፈ ሃሳብ ባሻገር ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ብለዋል።

በሥርዓተ ትምህርቱ የተደረገው ማሻሻያ ተማሪዎች እንደየተስጧቸው በአይ.ሲ.ቲ.፣ በእርሻ፣ በኪነጥበብና መሰል የትምህረት መስኮች የዳበረ ሙያዊ ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

ሥርዓተ ትምህርቱን ምንም እንኳን በአንዴ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ባይቻልም በሙከራ ደረጃ ስኬታማ እንደሆነ ገልጸዋል።

40 የሚደርሱ የትምህርት አይነቶችን ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በሚቀጥለው ዓመት 12 የሚደርሱት የትምህርት አይነቶች መሰጠት ይጀምራሉ ብለዋል።

በሕትመት ዝግጅት ሂደቱም በጊዜያዊነት ማስተማር የሚቻልባቸው 13 የትምህርት አይነቶች የመጽሃፍት ሕትመት መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በቀጣይም ሁሉንም አይነት የትምህርት አይነቶች በተሟላ ሁኔታ ማስጀመር የሚስችል የመጽሃፍት ሕትመት ይደረጋል ብለዋል።

የበጀት እጥረት የመጽሃፍት ህትመቱ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ቢሆንም በተለያየ መንገድ የመጽሃፍት ህትመቱን ለማከናወን ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም