የውኃና የኃይል አቅርቦትን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶችን ትብብርና ተሳትፎ እንሻለን- ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ - ኢዜአ አማርኛ
የውኃና የኃይል አቅርቦትን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶችን ትብብርና ተሳትፎ እንሻለን- ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የውኃና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት የአጋር ድርጅቶች ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ ጠየቁ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃና የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ዙሪያ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ፣ የክልል ቢሮ ኃላፊዎች፣ የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ነው?፣ምን ዓይነት ክፍተቶች አሉ? በቀጣይ ምን ላይ ማተኮር ይገባል በሚሉ ጉዳዮች በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ ውይይት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ መንግሥት በውኃና ኢነርጂ አቅርቦት ላይ ባለፉት ዓመታት አበረታች ሥራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የመጠጥ ውኃ አቅርቦቱ 68 በመቶ መድረሱን ጠቁመው በኢነርጅ ዘርፍም አፈጻጸሙ ከ51 በመቶ በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የውኃና ኢነርጂ አቅርቦት ላይ መንግሥት ከሚሰራቸው ተግባራት ባሻገር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየተሳተፉ ቢሆንም የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
በውኃና ኢነርጂ ልማት የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን የሚያስፈልገው ኃብት እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ ይሰበሰባል እንዴትስ ሥራ ላይ ይውላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ሥራ ያስፈልጋል ብለዋል።
የዜጎችን ህይወት የሚያሻሽሉ የውኃና ኢነርጂ አቅርቦት በተሳለጠ መልኩ እንዲቀርቡ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር መንግስት ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ማሞ፤ የውኃ ልማትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አገልግሎት ፈላጊው እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጀት ብዙ ስራ የሚጠበቅ በመሆኑ ለዚህም በቅንጅት መስራት ይገባል ብለዋል።
የቪታ ግሪን ኢምፓክት ፕሮግራም ተወካይ ሱልጣን አብዱራህማን፤በተለይ በኢነርጂው አቅርቦት ላይ የቴክኖሎጂ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት ይፈልጋል ብለዋል።
በኃይል አቅርቦት ላይ የተሰማሩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚገጥሟቸውን ችግሮች መፍታት ዜጎችን የበለጠ ለማገልገል ቁልፍ መሆኑን ጠቁመው ከሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ ይፈልጋል ሲሉም ገልጸዋል።
ከኖርዌይ ዕርዳታ ድርጅት የተወከሉት ጌዲዮን ተካ፤ በውኃና ኢነርጂ አቅርቦት መስክ ከሚኒስቴሩ ጋር የተናበበ ሥራ መስራት የሚያስችል ወጥ የሆነ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ተናግረዋል።