በበጀት ዓመቱ የስራ እድል ፈጠራን፣ የክህሎት ልማትና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ስራን በተለየ እሳቤ በመከናወን ላይ ነው- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የስራ እድል ፈጠራን፣ የክህሎት ልማትና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ስራን በተለየ እሳቤ በመከናወን ላይ ነው- የስራና ክህሎት ሚኒስቴር
ሰመራ ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ በ2016 በጀት ዓመት የስራ እድል ፈጠራን፣ የክህሎት ልማትና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ስራን በተለየ እሳቤ በማከናወን ላይ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ዛሬ በሰመራ ከተማ የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የስራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት በ2016 በጀት ዓመት ያለፉትን አሰራሮች በመፈተሽ አዳዲስ እሳቤዎችን በስራ ዘርፎች በሚያሰርጽ መልኩ ወደ ስራ መገባቱን አንስተዋል።
በተለይም የስራ እድል ፈጠራን፣ የክህሎት ልማትና የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ስራን በተለየ እሳቤ ለማከናወን ታቅዶ በፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በብቃት ምዘና ማዕከላት፣ በአንድ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችና በኢንተርኘራይዞች የሱፐርቪዥን ቡድን ተሰማርቶ ተገቢው ክትትልና ግምገማ ተደርጓል ብለዋል ።
በተለይም ስራን በክህሎት መር በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በርካታ ስኬቶችን እንዲያስመዝግቡ እያገዛቸው መሆኑን በማከል።
መድረኩ በግምገማ ብቻ የማይወሰን መሆኑን ጠቅሰው መድረኩ በየዘርፉ የተሰሩ ስራዎችንና አጠቃላይ የስድስት ወራት ጉዟአችንን ገምግመን ስኬቶቻችንን ለማስቀጠልና ፈተናዎችን ለማረም የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተጨባጭ ስኬቶችንና ዕጥረቶችን ለይተን ጥንካሬያችንን የምናስቀጥልበት፣ የታዩ ዕጥረቶችን ለመፍታት ደግሞ ቃል የምንገባበት መድረክ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በበኩላቸው አገራችን በአሁኑ ወቅት ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ስራ ፈጣሪ ዜጋ የምትሻበት ጊዜ ነው ብለዋል።
"አገራችን አንድነቷ የተጠበቀ፣ የበለፀገችና የተከበረች ሐገር ናት" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዋናነት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከስደት ማላቀቅና በግልም ሆነ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት ይገባናል ብለዋል።
ድህነትን የምትሻገር የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ስራን በክህሎት መምራቱ ወሳኝና ግንባር ቀደም መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድር አወል አስረድተዋል።
"ስራ በክህሎት ይመራ" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ባለው መድረክ ባለፉት 6 ወራት ሀገራዊ የክህሎት ልማት ስራ እድል ፈጠራ እና የኢንዱስትሪ ሰላም ግንባታ ላይ የተሰሩ ስራዎችን ከመገምገም ባለፈ የቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ይመክራል።
በመድረኩ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና የአመራር አባላት፣ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባን ጨምሮ የሁሉም ተጠሪ ተቋማት አመራር አባላት፤ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እና የአሰሪና ሰራተኛ ቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።