ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ ተደረገ

ጋምቤላ ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦  በጋምቤላ ክልል የሙቀት መጠን እየጨመረ በመምጣቱ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና ካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፒተር ሆው ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የሙቀቱ መጠን እየጨመረ በመምጣቱና ለስራ ምቹ ባለመሆኑ ከነገ የካቲት 1 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ ለሶስት ወራት የሚቆይ የመንግስት የስራ ሰዓት ለውጥ ተደርጓል።

በለውጡ መሰረትም ቀደም ሲል ከጧቱ አንድ ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ተኩል የነበረው ከአንድ ሰዓት እስከ አምስት ሰዓት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል።

እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከዘጠኝ ሰዓት እስከ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል የነበረው ከአስር ሰዓት እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ተኩል እንዲሆን ተወስኗል" ብለዋል።

የስራ ሰዓት ለውጡ ወይናደጋ የአየር ንብረት ያላቸውን የመንጌሽና የጎደሬ ወረዳዎችን እንደማይጨምር የገለጹት ኃላፊው የክልሉ የመንግስት ሰራተኞች በተጠቀሰው ጊዜ ወደ ቢሮ በመግባት የተለመደውን ስራቸውን  እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት የጋምቤላ ክልል የሜትሮዎሎጂ አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋሁን ዓለሙ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የክልሉ አማካይ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን 40 ዲግሪ ሴልሸስ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንዲሁም የሌሊቱ ዝቅተኛው መጠን ደግሞ 21 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሸስ መድረሱን ጠቁመው ባለፉት ወራት የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከ35 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሸስ፤ የለሊቱ ደግሞ 20 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴልሸስ   በታች እንደነበር ገልጸዋል።

በክልሉ የሞቃታማ ወራት የሚባሉት የካቲት፣ መጋቢትና ሚያዚያ ወራት ሲሆኑ በእነዚህ ወራት ውስጥ የቀኑ ከፍተኛ የሙቀት መጠን እስከ 45 ዲግሪ ሴልሸስ የሚደርስበት ጊዜ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም