ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ለትግራይ ክልል 67 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብና የመድኃኒት ድጋፍ አደረገ

መቀሌ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ለትግራይ ክልል 67 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብና የመድኃኒት ድጋፍ አደረገ።

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ድጋፉን ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ  ዛሬ አስረክበዋል። 

ጠቅላይ ምክር ቤቱ በጠቅላላው 67 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የእህል እንዲሁም የተለያዩ መድኃኒቶችና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼኽ ኢብራሂም ቱፋ ለወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ተናግረዋል። 

''አንድነታችንን እና ፍቅራችንን ለመግለፅ በክልሉ ለተቸገሩ ወገኖች የሚውል ድጋፍ ይዘን መጥተናል፤ በቀጣይም በምንችለው ሁሉ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ ነን'' ብለዋል። 

ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። 

''ከትግራይ ወንድሞቻችን ጋር በአካል ተገኝተን ግንኙነታችንን ማጠናከር፣ ድጋፍም ማድረግ አለብን ብላችሁ መምጣታችሁ ትልቅ መልእክት ነው'' ያሉት አቶ ጌታቸው ፣ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም