ቀጥታ፡

ማህበሩ በሰሜን ሸዋ ዞን  ለህክምና ተቋማት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት መድሃኒት ድጋፍ አደረገ

ደብረ ብርሀን ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሰሜን ሸዋ ዞን ለሚገኙ የህክምና ተቋማት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መድሃኒት ድጋፍ አደረገ። 

በማህበሩ የደብረ ብርሀን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው እንደገለጹት፤ የተደረገው የመድሀኒት ድጋፍ ከዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር የተገኘ ነው።

ድጋፉ  በነበረው ችግር ምክንያት የህክምና መድሀኒት አቅርቦት እጥረት ላጋጠማቸው አስር ሆስፒታሎችና ስድስት ጤና ጣቢያዎች የሚውል መሆኑን  ተናግረዋል።

ይህም የጤና ተቋማቱ ያጋጠማቸውን የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት በማቃለል  ተገቢውን ህክምና ለመስጠት እንደሚያግዝ  አመልክተዋል።

መድሀኒቱ የተለያየ ዓይነት መሆኑንና ከ30 ሚሊዮንብር በላይ ግምት እንዳለው ጠቅሰው፤ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ በበኩላቸው፤ በነበረው ችግር ሳቢያ ለጤና ተቋማቱ ተገቢውን መድሃኒት ገዝቶ ማቅረብ ባለመቻሉ እጥረት አጋጥሞ መቆየቱን ተናግረዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኩል የተገኘው የመድሀኒት ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በዞኑ ጊሸራቤል ወረዳ የግሼ ጤና ጣቢያ ተወካይ ወይዘሮ ሚሊዮን ግርማ፤  በአካባቢው ተፈጥሮ በቆየው ችግር  ምክንያት  የመድሃኒት አቅርቦት እጥረት አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል።

ማህበሩ ለጤና ጣቢያው ያደረገው ድጋፍ  ችግሩን የሚያቃልልና ለህሙማን ተገቢውን ህክምና ለመስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም