ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መሳካት በኢትዮጵያ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መሳካት በኢትዮጵያ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ መሳካት በኢትዮጵያ በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም፤ በወቅታዊ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በአዲስ አበባ ለሚካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በፕሬዝዳንቶች የሚመሩ 24 አገራትን ጨምሮ ከ34 በላይ አባል ሀገራት የሚሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ ቀናትም የሚያሳውቁ ተሳታፊ ሀገራት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ለጉባዔው መሳካት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሁሉ ዝግጅት አድርጋ ማጠናቀቋን ገልጸዋል።
ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ለሁለትዮሽና ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳይ ትኩረት ታደርጋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በ77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰቆጣ ቃል ኪዳንና የአረንጓዴ አሻራ አጀንዳ ቀርፃ አቅርባ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በራሷ ሀሳብ አመንጭነት ለአፍሪካና ለዓለም ልምዶቿን የምታካፍልበት አጀንጻ ቀርፃ እንደማታውቅ አስታውሰዋል፡፡
በዘንድሮው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትናዋ መረጋገጥና ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የሰጠችውን ትኩረት በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ የሚካሄድ የጎንዮሽ መድረክ ይኖራታል ብለዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂን በሚገባ በመጠቀም ልማትን ማሳለጥ ኢትዮጵያ በመሪዎች ደረጃ የምታዘጋጀው ሁለተኛው የጎንዮሽ ስብሰባ መሆኑንም ገልፀዋል።
የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን 44ኛው የአባል ሀገራቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዘንድሮው የ2024 በጀት ዓመት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ እቅድ አጀንዳዎችን መቅረፅ ልምዶችን ማካፈልና ሌሎች እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ስለመሆኑም አምባሳደር መለስ አንስተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ተደማጭነትና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን የሚያረጋግጡ አጀንዳዎችን ቀርፃለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነትና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጥረት ስኬታማ ሳምንት ማሳለፏን የገለጹት አምባሳደር ዶክተር መለስ ዓለም ጥረቷ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ የኢትዮ ሩሲያ የፖለቲካና ቢዝነስ መድረክ፣ የኢትዮ ጅቡቲ 127ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተመለከተ የነበረው ሁነት ከሳምንቱ አበይት ጉዳዮች መካከል እንደነበሩ ጠቅሰዋል።