ታንዛንያ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች

1298

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ ታንዛንያ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጓ ተገለጸ፡፡

ስፑትኒክ ድረገጽ የአገሪቱን ምክትል ፕሬዝደንት ቢሮ ጠቅሶ እንደዘገበው ታንዛንያ ከተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2023 ወዲህ 35 የካርበን ሽያጭ ማመልከቻዎችን ተቀብላለች፡፡  

በቢሮው የአካባቢ ደህንነት ኃላፊ ሴሌማኒ ጃፎ እንደተናገሩት የካርበን ሽያጭ ለአገሪቱ የገቢ ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡

የካርቦን ሽያጭ  ከ2018 እስከ 2022 ባሉት አመታት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የተተገበረው የካርበን ሽያጭ ለአገሪቱ ከ12 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን ተናግረዋል።

“የካርቦን ሽያጭ የታንዛንያን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማገዝና የተፈጥሮ አካባቢን ለመንከባከብ የራሱ አስተዋጽኦ አለው“ ያሉት ሴሌማኒ ጃፎ ጠቀሜታውን ለህብረተሰቡ በማስረዳትና በስፋት በማሳተፍ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

በዱባይ በነበረውም  የኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉዳዮች ጉባኤ ላይ የሃገራቸውን መልካም ተሞክሮ በማቅረብ ዘርፉ ላይ ከሚሰሩ አካላት አዎንታዊ ግብረመልሶች ማግኘት መቻሉን አላፊው ገልጸዋል፡፡

በተገኘው ውጤትም ታንዛንያ የአንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን  ተናግረዋል፡፡

ታንዛንያ ከሶስት አመታት በፊት ብሔራዊ የካርበን ሽያጭ መመሪያ በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት እንዲመሩበት ማድረጓ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፍ እያከናወነች ባለው ሥራ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅዳ እየሰራች ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም