ኢትዮጵያን በብቃት፣ በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል የሚችሉ ዜጎችን በካቢኔ ውስጥ የማካተት ስራ ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን በብቃት፣ በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል የሚችሉ ዜጎችን በካቢኔ ውስጥ የማካተት ስራ ይቀጥላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በብቃት፣ በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል የሚችሉ ዜጎችን በካቢኔ ውስጥ የማካተት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ/ር ) ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ15ኛ መደበኛ ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቀረቡለትን የአስፈጻሚ አካላት ሹመት አጽድቋል።
በሹመቱም ተመስገን ጥሩነህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም ዶክተር መቅደስ ዳባ የጤና ሚኒስትር ሆነው በመሾም ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ለምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ሚኒስትሮቹን ለመሾም ላለፉት ሶስት ወራት የብልጽግና ከፍተኛ አመራር መክሮበታል ብለዋል።
በሂደቱም በርካታ እጩዎች ከተለዩ በኋላ ሀገሩን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ እስከሆነ ድረስ እንዲሾም መግባባት ላይ መደረሱን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተለመደ መልኩ የተፎካከሪ ፓርቲ አመራሮች በሚኒስትርነትና የተለያዩ ሃላፊነቶች ተሹመው እያገለገሉ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም ተመሳሳይ አድሎች የሚሰጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የብልጽግና ፓርቲ አባል ባይሆኑም ሀገራቸውን በቅንነትና በብቃት ለማገልገል የሚችሉትን በተለያዩ ሃላፊነቶች መሾማችን ይቀጥላል ብለዋል።
ከአለም አቀፍ ተቋማትና ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር በተለያዩ ሃላፊነቶች ኢትዮጵያን ለማገልገል ብቃት ያላቸውን ዜጎች የማሳተፉ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት በመገንባት ሂደት ሁሉም ተሳትፎ በማድረግ የድርሻውን መወጣት አንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።