ቀጥታ፡

የጃፓኗ ካሳማ ከተማ ከንቲባ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ የጃፓኗ ካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የስፖርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ፌዴሬሽኑ አስታወቀ።

በጃፓን ካሳማ ከተማ ላለፋት ተከታታይ አምስት ዓመታት በታሕሳስ ወር ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ በቂላን የሚዘክር የግማሽ ማራቶን ውድድር ሲዘጋጅ መቆየቱም በዚሁ ወቅት ተመላክቷል፡፡

ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ዛሬ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተለያዩ የስፖርት ትጥቅ ድጋፎችን ያስረከቡ ሲሆን በዚህም መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ትጥቆቹ የተሰበሰቡት በ2023 በካሳማ በተካሄደው የአበበ በቂላ መታሰቢያ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አካላት መሆኑን ጠቁመው በየዓመቱ ድጋፉ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ(ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡


 

በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው ጃፓን እና ኢትዮጵያ 100 ዓመት የሚጠጋ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመርሐ- ግብሩ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የካሳማ ከተማ ከንቲባ ሺንጁ ያማጉቺ ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም