የኢትዮጵያ የትምህርት ማሻሻያ ስራ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው- የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የትምህርት ማሻሻያ ስራ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ነው- የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የትምህርት ማሻሻያ ስራ በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚያስችላት መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሐመድ ቤልሆሲን ገለጹ።
በአፍሪካ የትምህርት ፖሊሲ ምክክሮች ዙሪያ የኢትዮጵያን የነቃ ተሳትፎም ኮሚሽነሩ አድንቀዋል።
የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓት ስብራት ለመጠገን መንግስት የማሻሻያ ስራዎችን እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።
አዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ፣ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማትና የትምህርት ግብአቶችን ማሟላት፣ የመምህራን አቅም ማጎልበትና የብቃት ምዘና ፍተሻ ከማሻሻያዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።
የትምህርት ሚኒስቴርም “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል ሀገር አቀፍ የሕዝብ ንቅናቄ ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።
በንቅናቄው መሰረትም የመጀመሪያ፣ መካከለኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የመሰረተ ልማት ጉድለቶች የማሻሻል ስራ እየተሰራ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የትምህርት፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መሐመድ ቤልሆሲን፤ የኢትዮጵያ የትምህርት ማሻሻያዎች የሚደነቁና በአጭር ጊዜ ለውጥ የሚያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
በትምህርት ስርዓቱ ለውጥ ለማምጣት እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች መልካም ጅምሮች መሆናቸውን ጠቅሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራ በማከናወን ለውጥ ለማምጣት ያስችላታል ብለዋል።
የትምህርት ዘርፉ ሕጻናትና ታዳጊዎችን እውቀት ማነስ እንዲላቀቁ በማድረግ የአፍሪካ አህጉር ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑንም ነው ፕሮፌሰር መሐመድ ያመለከቱት።
በአፍሪካ ትምህርትን አስመልክቶ በሚደረጉ የፖሊሲ ምክክሮች ላይ ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ ከሚያደርጉ አገራት መካከል እንደምትጠቀስም ገልጸዋል።
እ.አ.አ በ2022 የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ቀጣይ እጣ ፈንታን በተመለከተ የሚነጋገር የባለሙያዎች ቡድን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ሊቀመንበር አድርጎ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከውይይቱ በመነሳት ኢትዮጵያ ጽንሰ ሀሰቦች ወደ ተጨባጭ እውነቶች ለመለወጥ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአባል አገራቱ ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን ፕሮጀክቶችና
ማዕቀፎችን በመቅረጽ በትምህርቱ መስክ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም 44ኛውን የሕብረቱን የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብስባ እንዲሁም የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም 37ኛውን የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ያካሄዳል።
የሕብረቱ ጉባኤ እና የ2024 መሪ ሃሳብ "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት የሚል ነው።