ቀጥታ፡

በውጭ ግንኙነትና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነትና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስኬታማ ስራዎችን እያከናወነች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም(ዶ/ር)፤ በወቅታዊ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኃን ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የኮሞሮስ ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ የኢትዮ ሩሲያ የፖለቲካና ቢዝነስ መድረክ፣ የኢትዮ-ጅቡቲ 127ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በተመለከተ የተደረገው ዝግጅት ካሳምንቱ አበይት ጉዳዮች መካከል እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነትና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጥረት ስኬታማ መሆኗንም ገልጸዋል።

በቀጣይ በሚካሄደው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ ለሁለትዮሽና ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይ ትኩረት ታደርጋለች ብለዋል።

ለ37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔም በፕሬዝዳንቶች የሚመሩ 24 ሀገራትን ጨምሮ ከ34 በላይ አባል ሀገራት በጉባኤው የሚሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ቀናትም የሚያሳውቁ ተሳታፊ ሀገራት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው ለጉባዔው መሳካት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሥራ ማጠናቀቋን ገልጸዋል።

ከሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ባሻገር ኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትናዋ መረጋገጥና ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የሰጠችውን ትኩረት በተመለከተ በመሪዎች ደረጃ በሚካሄድ መድረክ ይኖራታል ብለዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂን በሚገባ በመጠቀም ልማትን ማሳለጥ ኢትዮጵያ በመሪዎች ደረጃ የምታዘጋጀው ሁለተኛው የጎንዮሽ ስብሰባ መሆኑንም ገልፀዋል።

37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ 44ኛው የአባል ሀገራቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ ከመሪዎች ጉባዔ ቀደም ብሎ የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም