የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ድጋፍ የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው
ሮቤ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ እያደረገ የሚገኘውን ጥረት እየደገፈ መሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
ማህበሩ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የገዛውን አምቡላንስ ለሮቤ ከተማ አስተዳደር አስረክቧል፡፡
የአምቡላንስ ድጋፉ በተለይም ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስና መሰል የነፍስ አድን ስራዎችን ለማከናወን የነበረውን ውስንነት እንደሚያሻሻል ተመላክቷል፡፡
በድጋፍ ርክክቡ ስነስርዓት ወቅት በማህበሩ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ተሾመ አባቡ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች በሚከሰቱ ችግሮች የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እየሰራ ነው፡፡
በተለይም ማህበሩ መንግስት የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ እያደረገ የሚገኘው ጥረት እንዲሰምር የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ማህበሩ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በመግዛት ለከተማ አስተዳደሩ በድጋፍ የሰጠው አምቡላንስ ለነፍስ አድን ለሚሰራው ስራ ማሳያ እንደሆነ በማንሳት፡፡
አቶ ተሾመ እንዳሉት ማህበሩ ከዚህ በፊት በከተማ አስተዳደሩ መድሃኒት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህዝብ የሚያቀርብ መድኃኒት ቤት ከፍቶ ለአገልግሎት ማብቃቱንም አስታውሰዋል፡፡
በቀይ መስቀል ማህበር በኩል ለአገልግሎት የቀረበው አምቡላንስ ለታለመለት ዓላማ ብቻ ሊውል እንደሚገባም አቶ ተሾመ አሳስበዋል።
በርክክቡ ወቅት የተገኙት የሮቤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ በበኩላቸው ማህበሩ ለነፍስ አድን ስራ ቅድሚያ መስጠቱ ተገቢነት ያለውና የሚደነቅ ነው" ብለዋል።
በድጋፍ የተገኘው አምቡላስ በከተማ አስተዳደሩ በአምቡላንስ እጥረት ምክንያት ሲፈጠር የነበረውን ክፍተት ለማሻሻል ስለሚረዳ ማህበሩን አመሰግነዋል፡፡
ድጋፉ ማህበሩ በከተማው በሶስት አምቡላንስ ብቻ ሲሰጥ የነበረውን የነፍስ አድን ስራ ወደ አራት አምቡላንሶች ያሳድገዋል ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሲስተር ማህፉዛ ጀማል ናቸው፡፡
የአሰተዳደሩን የጤና አገልግሎት በማሻሻል በኩል እገዛው ከፍተኛ በመሆኑ ማህበሩን አመስግነዋል፡፡
ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ሀሰን በሰጡት አስተያየት ከከተማው የህዝብ ብዛት የተነሳ የነበረውን የአምቡላንስ አገልግሎት መጨናነቅ እንደሚያቃልል አንስተዋል፡፡