ቀጥታ፡

የባህር በር የመግባቢያ ስምምነቱ ፓንአፍሪካኒዝምን የሚያጎለብትና ቀጣናዊ ውህደትንና የጋራ ልማትን የሚያፋጥን ነው-የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ምሁራን

አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገችው የባህር በር የመግባቢያ ስምምነት የፓንአፍሪካንዝም እንቅስቃሴ የሚያጎለብት የጋራ ልማትና ሰላምን በማረጋገጥ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያፋጥን መሆኑን የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር )ከሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ጋር ኢትዮጵያ የባህር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት ታህሳስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ መፈራረማቸው ይታወቃል።

ስምምነቱን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ ምሁራን ስምምነቱ ከሁለቱ ወገኖች አልፎ ቀጣናዊ ትስስርን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም፤ ኢትዮጵያ ለዘመናት የነበራትን የባህር በር በመጥፎ አጋጣሚ ማጣቷን አስታውሰው አሁን ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት አማራጭ ወደብና የባህር በር ለማግኘት በዓለም አቀፍ ህግና በሰጥቶ መቀበል ዲፕሎማሲያዊ መርህ ላይ በመመስረት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኗን ጠቅሰዋል።

ከሶማሌላንድ ጋር የተደረገው የመግባቢያ ስምምነትም የጋራ ተጠቃሚነትን፣ አካታች ልማትንና ሰላምን በቀጣናው ለማረጋገጥ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመሆኑም በአካባቢው ሀገራት የሚኖረው ማህበረሰብ ስምምነቱ ይዞት የሚመጣውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ተገንዝቦ ለተፈጻሚነቱ እንዲሰራ በአርዓያነት መምራት ይገባል ብለዋል።


 

በሀርጌሳ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የግጭት ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪው አብዱራህማን መሐመድ በበኩላቸው ቀጣናው ውስን ሀብት፣ ተደራራቢ ሰው ሰራሽና የተፈጥሯዊ አደጋዎች የማይለዩት፣ ኃያላን የሚሻኮቱበት የመሆኑን ያህል የጋራ እጣ ፈንታቸው የማይነጣጠሉ ህዝቦች የሚኖሩበት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአካባቢው ካሉ ሀገራት ጠንካራ ኢኮኖሚና ትልቅ የህዝብ ቁጥር እንዳላት ጠቅሰው፤ በቀጣናው ሰላም እንዲመጣና ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲጠናከር በፋና ወጊነት እየሰራች ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ሲባል ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄም ቅቡልነት ያለውና ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና የሚጫወት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነትም ድንበር ዘለል ወንጀሎችን ለመከላከል፣ የባህር ውንብድናን ለመቆጣጠር፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ለሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ፣ ሶማሌላንድም ኢንቨስትመንትን እንድታስፋፋ፣ ለዜጎቿ ተጨማሪ የስራ እድል እንድትፈጥር ያግዛል ነው ያሉት።

የአፍሪካውያንን አንድነትና የጋራ መሻትን የሚመልስ፣ የፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ መሆኑን ጠቅሰው የአፍሪካ ህብረት ለያዘው ቀጣናዊ ውህደትም ጉልህ አስትዋፅኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።


 

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ መምህርት ህሊና አሸናፊ፤ ቀጣናዊ ትስስርን ለማረጋገጥ ኢኮኖያዊ ትብብር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ሰላም የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በመገንዘብ ለዚህም ሁሉም ሀገራት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ አንስተዋል።

በቀጣናው ፍትሐዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥም ለጋራ ህልውና መሰረት መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ወጪ ለማስተካከል በቀጣናው ያላትን በጎና የመሪነት ተፅዕኖ ለማጠናከርም ትልቅ አቅም ይፈጥራል ነው ያሉት።

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስን ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰር ሚፍታህ መሐመድ፤ ኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ፣ የልማት አቅም እና እምቅ ሀብት ያላት መሆኑ በቀጣናው ተፅዕኖ ለመፍጠር ያስችላታል ብለዋል።


 

ሌሎች ጎረቤቶቿ ደግሞ የባህር በር ያላቸው መሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር በሰጥቶ መቀበል መርህ ቀጣናውን ለማልማትና መረጋጋት እንዲሰፍንበት ማድረግ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ሀገራት በተናጥል ከሚያደርጉት የእድገት ጉዞና ውስን ሀብትን ለመቀራመት ከመሻኮት ወጥተው የጋራ የአብሮነት ርዕይና የተሻለ ቀጣና የመፍጠር ትልም ላይ ቢያተኩሩ ለትውልዱ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን መምህር ደመላሽ መንግስቱ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የባህር በር የሌላት መሆኗና አማራጭ ወደብ ባለመኖሩ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚ ዕድገት መሸከም የሚችል የወደብ አማራጭ ለመፈለግ መገደዷን ተናግረዋል።


 

ከሶማሌላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባር ሲገባ የኢትዮጵያን የወደብ አማራጭ በማስፋትና በአካባቢው ያላትን ሚና በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ሶማሌላንድም የአፍሪካ ኩራት ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ የሚኖራት መሆኑ ተጠቃሚነቷን በእጅጉ ያሳድገዋል ነው ያሉት።

ሆኖም ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠውን የመግባቢያ ስምምነት ወዳልተገባ ሁኔታ እየወሰዱ ያሉ አካላት በመኖራቸው ምሁራን ትክክለኛውን ሁኔታ የማስገንዘብ ግዴታ አለባቸው ብለዋል።

ለቀጣናው ትብብርና ሰላም አምባሳደር ሆነው መስራት እንደሚጠበቅቸው በመጠቆም።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም