ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃዎችን ለአገራትና ድርጅቶች መሸጥ ልትጀምር ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሕዋ ንግድ የሳተላይት መረጃዎችን ለአገራትና ድርጅቶች መሸጥ የሚያስችላትን አገልግሎት ዛሬ በይፋ አስጀምራለች።

የመረጃው ሽያጭ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የሚያስገኝ እንደሆነም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የሳተላይት መረጃውን የምትሸጥበት አገልግሎት የሚሰጠው በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ያስገነባው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ፣ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች አገልግሎቱን በይፋ አስጀምረዋል። 

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል ያስገነባው የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያ ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም መመረቁ የሚታወስ ነው።

ሶስት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተደረገበትና 7 ነጥብ 3 ሜትር ከፍታ ያለው ጣቢያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

ጣቢያው የሳተላይት መረጃዎችን የማከማቸት፣ የመተንተንና ወደ ምስል የመለወጥ ስራ የሚከውን ሲሆን ከመሬት ምልከታ ሳተላይቶች እስከ 0 ነጥብ 5 ሜትር የምስል ጥራት ያለው የሳተላይት መረጃ መቀበል የሚችል ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ይሽሩን አለማየሁ ኢንስቲትዩቱ በሳይንስ ዘርፉ ተጨባጭ እድገት እንዲመጣ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ጣቢያውን በመጠቀም የሳተላይት መረጃ አገልግሎት ለአገራትና ለድርጅቶች በመስጠት  ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን ሁኔታ መፍጠሩ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኢኒስቲትዩቱ በስፔስ ሳይንስ ዘርፉ ለውጥ ለማምጣት ለሚያከናውናቸው ተግባራት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። 

የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያው ከተለያዩ ሳተላይቶች የሚያገኛቸውን መረጃዎች እስከ አሁን ለአገር ውስጥ አገልግሎት ይውሉ እንደነበር ገልጸዋል።


 

ኢኒስቲትዩቱ የአገልግሎት ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያስችሉ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አመልክተዋል።

በዚሁ መሰረት የተለያዩ አገራትና ድርጅቶች ኢትዮጵያ ባላት የመሬት የመረጃ መቀበያ ጣቢያ አማካኝነት ከሳተላይቶች መረጃዎችን ማግኘት የሚያስችላቸውን አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ የመሬት መረጃ መቀበያ ጣቢያ የሌላቸው እንዲሁም የመሬት መረጃ መቀበያ ጣቢያ ኖሯቸው ተደራሽነታቸው ሰፊ ያልሆኑ የተለያዩ አገራትና ድርጅቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

መረጃ ተቀባይ አካላት የሳተላይት መረጃዎችን በ"ክላውድ ሰርቨር" አማራጭ እንደሚያገኙ በመጠቆም።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ ባለሙያዎች በሚሰጡት አገልግሎት የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የምትችልበትን አማራጭ ጭምር እንደሚሰጥ ነው አቶ አብዲሳ ያብራሩት።

ጣቢያው ምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የሚያካልልና መረጃዎችን የመሰብሰብ አቅም እንዳለው አስረድተዋል።

አገልግሎቱ ጣቢያው የሚቀበላቸውን የሳተላይት መረጃዎች ለአገራትና ለድርጅቶች መላክ እንደሚያስችል ገልጸው፤ የአገር ውስጥ ተቋማት መረጃዎችን ለማግኘት የሚያወጡትን የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀርም አመልክተዋል።

ጣቢያው ለ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የብዝሃ ሳተላይት መረጃ መቀበያና መቆጣጠሪያ ጣቢያው ከ11 ሳተላይቶች ተልዕኮ በመቀበል፤ መረጃ የመሰብሰብና ለሚፈለገው አካል መረጃ የሚልክበት የቴክኖሎጂ አሰራር እንደተዘረጋለት ተገልጿል።

የጣቢያው ዓላማ የኢትዮጵያን የሳተላይት መረጃ አጠቃቀም ማሳደግና መረጃዎቹን አገሪቱ በልማት ስራዎች እንድትጠቀም ማስቻል መሆኑ ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም