ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ አስፈጻሚ አካላት ከህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገነዘበ

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ አስፈጻሚ አካላት ከህዝብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስገነዘበ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክረምት ወራት በሕዝብ ውክልና ስራ አፈጻጸም ዙሪያ ከሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ያነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጣቸው ለሚመለከታቸው አስፈጻሚ አካላት አቅርበዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መሠረት ኃይሌ ህዝቡ ያነሳውን ጥያቄ ለአስፈጻሚ አካላቱ አቅርበዋል፡፡


 

በዚህም ከኑሮ ውድነትና ዋጋ ግሽበት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ህብረተሰቡን እየፈተኑ በመሆኑ ምላሽ እንዲያገኙ መነሳቱን ገልጸዋል፡፡

ከማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተገናኘም በስርጭት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ላይ ክትትል እንዲደረግ መጠየቃቸውንም አብራርተዋል።

ከስራ አጥነት ጋር የሚገናኙ ችግሮችም በዘላቂነት ለመፍታት አስፈጻሚው አካል ምን እየሰራ መሆኑንም ጠይቀዋል።

የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም በአንዳንድ የመስኖ፣ የመንገድ እና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታዎች ላይ የሚታዩ መጓተቶች መስተካከል እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የህዝብ ውክልና ስራዎቻቸውን በታማኝነትና ከክልሎች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

በህዝብ ውይይት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽ የሰጡት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፤ መንግስት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡


 

ለአብነትም 913 የእሁድ ገበያዎችን እንዲቋቋሙ በማድረግ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን እንዲያገኝ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው መንግስት የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡


 

ከዚህ ቀደም ግንባታቸው ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቀሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜ ከ27 በላይ የመስኖ ግንባታ እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በምላሻቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተዳራሽ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት 37 አዳዲስ ቀበሌዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ቱሉ በበኩላቸው ለገቢ አሰባሰቡ እንደ ተግዳሮት የሚነሱ ጉዳዮች ተለይተው ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የገቢ አሰባሰብን ለማሳደግም የደረሠኝ ስርዓቱን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ በዚሁ ወቅት መንግስት የኑሮ ውድነትን ለማሻሻል፣ የፕሮጀክት አፈጻጸምን ለማሳደግ እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

በሌላ መልኩም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የህዝቦችን የመልማት ጥያቄዎች ተቀብሎ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ እንዳሉትም የህዝብ ተወካዮች የውክልና ስራቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


 

ተመራጮች በዓመት ሁለት ጊዜ ወደ መረጣቸው ሕዝብ በመሄድ ከሕዝቡ ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን በውይይቱ ወቅት ከህዝብ የሚሰነዘሩ ጥያቄዎችን በማሰባሰብ በየደረጃው ለሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ምላሽ እንዲሰጥባቸው እንደሚደረግ የምክር ቤቱ የአባላትና የስነ-ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ያዛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም