የሕብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ማረጋጋት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሊደገፉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሕብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ማረጋጋት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ሊደገፉ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ ሕብረት ሥራ ማኅበራት የገበያ ማረጋጋት ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ መደገፍ እንደሚያስፈልግ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ገለጹ።
10ኛው ሀገር አቀፍ የህብረት የስራ ማህበራት አውደ-ርዕይና ሲምፖዚየም “የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ከገበያም በላይ” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ የሕብረት ሥራ ማኅበራት በአገሪቱ ገበያን በማረጋጋት በኩል ሚናቸው የጎላ ነው።
ማህበራቱ በገጠር ከማዳበርያ አቅርቦት እስከ ብድርና ቁጠባ፤ በከተማ ደግሞ የግብርና ምርትን በማገበያየት ዋጋን እስከ ማረጋጋት የላቀ ሚና እየተጫወቱ ነው ብለዋል፡፡
ዘርፉ በለውጥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ያሉትን ተግዳሮቶች በመፍታት የሕብረት ስራን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የማህበራቱ አቅም በማሳደግ የገበያ ዋጋን የሚቀበሉ ብቻ ሳይሆን ለመወሰን የሚችሉ እንዲሆኑ ለማድረግ በትብብር መስራት ያስፈልጋል።
ማህበራቱም ለምርት ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በማቅረብ ረገድ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉም እገዛ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።
በአሁኑ ወቅት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የግብርና ምርቶች እሴት ጥመራ ተግባራት ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ከተሰጣቸው መስኮች መካከል መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ጌታቸው መለሰ፤ በበኩላቸው የሕብረት ስራ ማህበራቱን የአሰራርና የአደረጃጀት ስርዓት ለመለወጥ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ይህም የኅብረት ሥራ ማሕበራትን የገበያ ድርሻ በማሳደግ ወደ ህብረተሰቡ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የሚያግዛቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
በዚህም የማህበራቱ ዋነኛ አላማ የሆነውን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት በመሠረታዊ የሸማቾች ኅብረት ስራ ማህበራት ከ474 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙን ገልጸዋል።
ማህበራቱ በምርት ግብይት ውስጥ በስፋት በመግባታቸው የዋጋ ንረትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።
ማህበራቱ በመዲናዋ የዋጋ ንረትን ለመከላከል አዎንታዊ ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በነገው ዕለት ከ250 በላይ አምራችና ሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ባዛር የሚጀመር ይሆናል፡፡