ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ ናት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ዝግጁ ናት
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚገጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩሏን ለመወጣት ዝግጁ ናት ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ተናገሩ።
20ኛው የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም የቡናዎች ማህበር ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ቡና ሳምንት ከመርሃ ግብሩ ጎን ለጎን በመካሄድ ላይም ይገኛል።
ጉባኤውና ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ፣ ኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽንና የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበር በጋራ አዘጋጅተውታል።
ዛሬን ጨምሮ ለሚቀጥሉት አራት ቀናት በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች፣ ቆዪዎች ፣ቡና አምራቾች ፣ የዘርፉ ባለሙያዎችና የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በመክፈቻው ላይ እንዳሉት በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም ችግሮች ይስተዋላሉ።
የተለያዩ በሽታዎች፣ በቂ ዝናብ ያለማግኘት፣ የዓለም የቡና ገበያ በየጊዜው መለዋወጥን ጨምሮ በአህጉሪቱ በቡና ልማት ዘርፍ እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎች በጋራ ለማለፍ በትብብር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚገጥሙ ችግሮችን በትብብር ለማስወገድ በሚደረገው አህጉራዊ ጥረት የድርሻዋን ለመወጣት ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በዘርፉ ያሉ ተዋንያንን ቅንጅት ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና አለው።
የኢትዮጵያን ምርታማነትን ለመጨመር ከአርሶ አደሩ፣ በዘርፉ ካሉ ተዋንያን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነውም ብለዋል።
መሰል አህጉራዊ ሁነት በኢትዮጵያ መካሄዱ ኢትዮጵያ በመስኩ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተዋንያንን የበለጠ የሚያቀራርብ የልምድ ልውውጥ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽን ዋና ጸሃፊ አምባሳደር ሶሎሞን ሩቴጋ በበኩላቸው የአፍሪካ ቡና ኢንዱስትሪ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ መሆኑን አብራርተዋል።
የቡና ምርት ላይ እሴት አለመጨመር፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ቡናን በሚፈለገው ደረጃ ያለማምረት ችግሮች ከፈተናዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አህጉራዊ ቅንጅቶች ሊጠናከሩ ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
በጉባኤና ኤግዚቢሽኑ ላይ ከ1 ሺህ በላይ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የቡናው ዘርፍ ተዋንያኖች በመሳተፍ ላይ ናቸው።