በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የልማት ትብብርን ለማጠናከር የወጣቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የልማት ትብብርን ለማጠናከር የወጣቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ የልማት ትብብርን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የወጣቶች ተሳትፎና የመሪነት ሚና እንዲጠናከር ተጠየቀ።
በፓን አፍሪካኒዝም እና ቀጣናዊ ትስስር ፅንሰ ሃሳቦች ዙሪያ ወጣቶች ስለሚኖራቸው ሚና በተመለከተ "ቀጠናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ፤ ቀጣናዊ ሰላም እና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ እና መስተጋብር ለማጠናከር የወጣቶች ሚና ጉልህ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በሉላዊነት ዘመን ቀጣናዊ ትስስር ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት የነገ ሀገር መሪ የሆኑ ወጣቶች የቀጣናዊ ውህደት ገንቢዎችና መሃንዲሶች እንደሆኑም አስረድተዋል።
በዚህም የጎረቤት አገራት ወንድማማችነት ስሜት በማጎልበት ረገድ ወጣቶች ሚናቸውን በላቀ ሁኔታ እንዲወጡ አቅማቸውን ማጎልበትና ምቹ ምህዳሩን መፍጠር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤትም የቀጣናው አገራትን በማሰባሰብ የመሪነት ሚናውን እንዲያጠናክር አሳስበዋል።
ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ በቅርቡ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ብሩህ ነገን ለመገንባት ሁነኛ የትብብር ማሳያ እንደሆነ ገልፀው፣ ስምምነቱ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ ያለውን ሚና አንስተዋል።
ስምምነቱ በዓለም መድረክ የጋራ ድምጽ ለማሰማትና የጋራ ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት ወጣቶች ለዘላቂ ሰላምና ልማት የመሪነት ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ፤ ወጣቶች ቀጣናዊ ትስስርን ለጋራ ብልፅግና እና ለበይነ መንግስታት ትብብር መጎልበት ቀዳሚ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ የባሕር በር ስምምነት የጋራ ሃብቶችን ለጋራ ጥቅም ለማዋል ያላቸውን የትብብር ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አመላክተዋል።
በመሆኑም ወጣቶች የአፍሪካን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ያላቸውን ሚና ተገንዘበው የተሳሰረ ክፍለ አህጉር ለመገንባት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና፤ ለቀጣናዊ ትስስርና ትብብር ብሎም ለዘላቂ ልማት ወጣቶች ድምጻቸውን ማጉላት እንዳለባቸው ገልጿል።
በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚነሱ የተዛቡ ትርክቶችን በማረም ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ መስራት አለባቸው ብሏል።
የኢትዮጵያና የሶማሌላንድ የመግባቢያ ሥምምነት ለሁለቱ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራት ሁለንተናዊ ልማት ያለውን ቁርጠኝነት የወጣቶች ምክር ቤት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑንም ጠቁሟል።