ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ህብረተሰቡን ለሚወክሉ ግለሰቦች ያዘጋጀው ስልጠና በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ

ጅግጅጋ ፤ ጥር 29 / 2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን በተባባሪ አካላት ተለይተው ህብረተሰቡን ለሚወክሉ ግለሰቦች ያዘጋጀው  ስልጠና  ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ ተጀመረ ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ እስካሁን አገራዊ የምክክር መድረክ ተሳታፊዎችን በሰባት ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የመለየት ስራ አከናውኗል። 


 

በተመሳሳይ መልኩ በሶማሌ ክልል በሁሉም ወረዳዎች  አገራዊ አጃንዳ ማሰባሰቢያ ላይ ለሚሳተፉ ተወካዮች እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 

የዛሬው መድረክ ጅግጅጋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በፋፈን ዞን  ከሚገኙ ወረዳዎች የተውጣጡ  የህብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተገኘወርቅ ጌጡ ናቸው።  


 

በዚህም ከመምህራን፣ የመንግሥት ሰራተኞች፣ አርብቶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአካል ጉዳተኞችና የሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች  ተወካዮች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። 

የስልጠናው  መድረክ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።

በቀጣይም በፊቅዞን፣ ደጋሃቡርና ሲቲ ዞኖች ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም