ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭዎች ድጋፍ ባቆሙበት ወቅት መንግስት ተጨማሪ ሀብት በመመደብ ዜጎቹን ከድርቅ አደጋ ታድጓል- የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016 (ኢዜአ)፦ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ አካላት ያለምንም ማስጠንቀቂያ ድጋፍ ባቆሙበት ወቅት መንግስት ተጨማሪ ሀብት በመመደብ ዜጎቹን ከድርቅ አደጋ መታደጉን  የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ድርቅና ሰብአዊ ድጋፍን የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳስሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን አንስተዋል።

መንግስት ከለውጡ ወዲህ በተለይ ከድርቅ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቋቋም ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ማተኮሩን ተናግረል።

መንግስት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በድርቅና ሌሎች አደጋዎች የሰው ህይወት እንዳያልፍ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

ሆኖም አንዳንድ አካላት ድርቁን ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

ከዚህ ይልቅ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰው ህይወት እንዳያልፍ መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ለተከሰተው የድርቅ አደጋ መንግስት አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍና የተቀናጀ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። 

የሰብአዊ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ባለፈው አንድ ዓመት ከግማሽ ገደማ የድጋፍ ምላሻቸው በመቀዛቀዙ ከ70 በመቶው በላይ በመንግስት አቅም መሸፈኑን ገልጸዋል።

ከሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎት አንጻር ባለፈው ዓመትም የተገኘው 33 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታውሰው መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት በ11 ቢልዮን ብር ወጭ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል እህል ገዝቶ አከፋፍሏል ብለዋል።

እርዳታ ሰጭዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ድጋፍ ባቆሙበት ወቅት መንግስት ተጨማሪ ሀብት በመመደብ ዜጎቹን መታደግ መቻሉን አስታውሰዋል።

በቀጣይም ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እንጂ ርሀብ አለመሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዓለም አቀፍ ተቋማት ጥናት እና በባለድርሻ አካላት ፈጣን ዳሰሳም ርሃብ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

በመሆኑም የተከሰተውን ድርቅ ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚ ለማዋል የሚደረግ ጥረት ተገቢ ያልሆነና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።

የድርቅ አደጋውን ተከትሎ የፌደራል መግስት የሰብአዊ ድጋፍና ፈጣን ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የክልሎችም ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።

በመንግስት እየተደረገ ያለው ድጋፍ በትክክል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረሱን የማረጋገጥ ስራ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም