የካፒታል ገበያ ፈቃድ የካቲት 04 ቀን 2016 ዓ.ም መሰጠት ሊጀመር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካፒታል ገበያ ፈቃድ የካቲት 04 ቀን 2016 ዓ.ም መሰጠት ሊጀመር ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ የካፒታል ገበያ ፈቃድ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም መስጠት እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ።
የካፒታል ገበያ ፈቃድ አሰጣጥ ቅድመ ዝግጅትና ተያያዥ የእቅድ አፈፃጸምን አስመልክቶ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ(ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በካፒታል ገበያ ዘርፍ ተለዋዋጭ ዕድገት እየመጣ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን በተያዘው ዓመት ለማስጀመር የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪዎች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር መመሪያ በማዘጋጀት ከየካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ፈቃድ መሰጠት እንደሚጀምር አስታውቀዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በካፒታል ገበያ ፈቃድ ማዕቀፍ ለመካተት ዝግጅት በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ እንደሚሰጥ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ጠንካራ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምኅዳር መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ለአብነትም ሶስት ትላልቅ የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡
የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሥራ የሚጀመሩበት ዕድል መፈጠሩም በዘርፉ ገበያ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አንስተዋል።
የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጪ የፈቃድ አሰጣጥ እና ቁጥጥር መመሪያ ሥራ ላይ መዋሉም ጠንካራ የቁጥጥር፣ የአስተዳደር እና የኢንቨስትመንት ጥበቃ ለማረጋገጥ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።
በሚቀጥሉት ስድስት ወራትም ቁልፍ ዓላማ እና ቅድሚያ የሚሰጠው የሥራ ሂደትን በማካተት የገበያ ታማኝነትን ማሳደግ፣ የክትትል ዘዴን ማጠናከርና የህግ ማስከበር ስራዎች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።
የኢንቨስተሮችን ግንዛቤ ማስፋት፣ ኢንቨስተሮችን ማብቃትና የፋይናንስ እውቀትን ማሳደግ፣ የካፒታል ገበያ ተሳታፊ ኩባንያዎችን ማበረታታት፣ አመቺ ሁኔታ መፍጠር እንዲሁም የፈቃድ አሰጣጥ ሂደትን ማቀላጠፍና የአሰራር ማዕቀፍ ላይ ግልጽነት መፍጠርም የትኩረት መስኮች እንደሆኑ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያን የመቆጣጠርና የማልማት ኃላፊነት ያለው ተቋም ሲሆን፤ ተልዕኮውም ኢኮኖሚያዊ እድገትንና ብልጽግናን የሚያጎለብት ግልጽ፣ ቀልጣፋና ለኢንቨስተሮች ተስማሚ ከባቢ መፍጠር ነው።