በ37ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ1 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በ37ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ1 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ በ37ኛዉ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ከ1 ሺህ በላይ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ጋዜጠኞች የሚዲያ ሽፋን ይሰጣሉ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ገለጸ፡፡
ጉባኤው የካቲት 09 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይታወቃል።
ባለስልጣኑ ጉባኤውን የሚዘግቡ የሀገር ዉስጥ እና የዉጭ ጋዜጠኞች የመግቢያ ባጅ እንዲያገኙ ለማድረግና ሁኑቱን ለመዘገብ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ የዉጭ ሚዲያ አካላት የመዳረሻ ቪዛ ለማመቻቸት እንዲሁም ለሙያ መሳሪያዎቻቸዉ የከስተም ክሊራንስ ስራዎችን ለማከናወን እንዲቻል እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እነዚህንም አገልግሎቶችም በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጉምሩክ፣ በአፍሪካ ህብረት ባጅ ሴንተር እና በባለስልጣኑ ዋና መስሪያ ቤት በቂ የሰዉ ኃይል በመመደብ 24 ሰዓት አገልግሎት በመሰጠት ላይ እንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡
ባለስልጣኑ የአፍሪካ ህብረት የብሔራዊ የጉባዔ አመቻች ኮሚቴ አባል ሆኖ በመሳተፍ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ እና ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ማግኘት እንዲችል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በሂደቱም ጉባዔዉን የሚዘግቡ ሚዲያዎች ቀልጣፋ አገልግሎት የሚያገኙበት፤ የሀገሪቱ እንግዳ ተቀባይነትና መልካም ገጽታ ጎልቶ በሚታይበት መልኩ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል።
በዚህም፤እስከ አሁን ባለዉ የምዝገባ ሂደት ከ350 በላይ የሃገር ዉስጥ እና 550 የዉጭ ጋዜጠኞች መመዝገባቸው ተጠቅሷል።
በቀጣይ ባሉት ቀሪ ቀናትም ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ጉባዔዉ በስኬት እንዲጠናቀቅ በላቀ ትጋት ሚናውን እንደሚወጣ ባለስልጣኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።