ምክር ቤቱ ነገ በሚያካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ ሹመቶችን ያፀድቃል - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ ነገ በሚያካሄደው 15ኛ መደበኛ ጉባዔ የተለያዩ ሹመቶችን ያፀድቃል
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ) 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ የአስፈጻሚ አካላት ሹመትን እንደሚያጸድቅ ተገለጸ፡፡
የምክር ቤቱን 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ እና 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ ጉባኤዎችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምክር ቤቱ በነገው ዕለት ከ1ኛ ልዩ ስብሰባ የተሸጋገሩ የተለያዩ አጀንዳዎችንም መርምሮ ያጸድቃል ተብሏል፡፡
ከተሸጋገሩት አጀንዳዎች ውስጥ የፌዴራል የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አዋጁን እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የሰራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብን በተመለከተ የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት እንዲሁም የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የሚቀርብ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ ይጠበቃል።