ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል- አምባሳደር ተፈራ ደርበው

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያና ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠሉን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ገለጹ።

 አምባሳደር ተፈራ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ኢትዮጵያና ቻይና ሁሉን አቀፍና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነትያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ የዲፕሎማሲ ዘርፎች ጠንካራ ትብብር መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

በተለይ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ የሁለቱ ሀገራት ትስስር በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፥ ቻይና በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንደምታንቀሳቅስ አንስተዋል።

በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢንቨስትመንት ፍቃድ እያወጡ እንደሚገኙም አንስተዋል።

በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲም የኢንቨስትመንት አማራጮችንና አመቺ ሁኔታዎችን ከማስተዋወቅ ጀምሮ ቻይናውያን ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች እንዲሳተፉ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያና ቻይና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲና ሌሎችም ዘርፎች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልኩ ግንኙነታቸው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

በንግድ ዘርፍ ኢትዮጵያና ቻይና የወጪና ገቢ ንግድ ልውውጣቸውን በከፍተኛ መጠን እያሳደጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ቻይና ያላትን ሰፊ የገበያ መዳረሻ በአግባቡ ለመጠቀም በኢትዮጵያ በኩል ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ለዚህም ወደ ቻይና ገበያ የሚላኩ ምርቶችን በዓይነትና በመጠን ለማሳደግ የቻይና አምራቾች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የወጪ ንግድ ምርቶች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ የተቀናጀ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ሀገራቱ በቱሪዝም መስክ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፉ የሰጠችውን ትኩረት በማስተዋወቅ ቻይናውያን መጥተው የመስህብ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ በማስተዋወቅ ላይ ነን ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ከተሞች በረራ የሚያደርግ በመሆኑ የቱሪዝም መስኩን ለማጠናከር ሰፊ እድል እንዳለው ጠቅሰዋል።

ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ባህልና እሴት የመጋራት ተሞክሮም እንዲኖር ሰፋ ያለ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.እ በ1970 የመሰረቱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ጠንካራና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂክ አጋርነት መሸጋገሩ ይታወቃል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም