ቀጥታ፡

20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ መካሄድ  ጀመረ

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦  20ኛው የአፍሪካ ባለ ልዩ ጣዕም የቡናዎች ጉባኤና ኤግዚቢሽን በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤውና ኤግዚቢሽኑ የኢትዮጵያ  ቡናና ሻይ ባለስልጣን ፣ኢንተር አፍሪካ ኮፊ ኦርጋናይዜሽንና የአፍሪካ ባለልዩ ጣዕም ቡናዎች ማህበር በጋራ አዘጋጅተውታል። 

ዛሬን ጨምሮ  ለሚቀጥሉት  አራት ቀናት በሚካሄደው መርሃ  ግብር ላይ  ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎች፣  ቆዪዎች፣ ቡና አምራቾች ፣ የዘርፉ  ባለሙያዎችና  የመንግሥት  የስራ ሃላፊዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። 

የግብርና  ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በመክፈቻው ላይ እንዳሉት በአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ቢኖሩም አሁንም ችግሮች ይስተዋላሉ። 

የተለያዩ  በሽታዎች፣ በቂ ዝናብ ያለማግኘት፣ የዓለም  የቡና ገበያ በየጊዜው  መለዋወጥን ጨምሮ  በአህጉሪቱ  በቡና ልማት ዘርፍ እየገጠሙ ያሉ ፈተናዎች  በጋራ ለማለፍ በትብብር  መስራት እንደሚገባ አጽንኦት  ሰጥተዋል። 

በዚህ ረገድ ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ በቡናው ዘርፍ  ተዋንያን  መካከል የዕውቀት  ሽግግር እንዲኖር  ለማድረግና የጋራ  መፍትሔ  ለማበጀት ቁልፍ ሚና አለው ብለዋል። 

የኢትዮጵያ  ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው ጉባኤና ኤግዚቢሽኑ  በዘርፉ ያሉ ተዋንያንን  ቅንጅት ለማጠናከር  ከፍተኛ  ሚና አለው። 

ኢትዮጵያ በቡና ሊለማ የሚችል እምቅ አቅም መኖሩን አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያን ምርታማነትን ለመጨመር ከአርሶ አደሩ፣ በዘርፉ  ካሉ ተዋንያን ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤  አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነውም ብለዋል። 

መሰል አህጉራዊ  ሁነት በኢትዮጵያ  መካሄዱ ኢትዮጵያ በመስኩ ያላትን አቅም ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።   

ከዚህ ባለፈ  በአፍሪካ  የቡና ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተዋንያንን የበለጠ የሚያቀራርብ የልምድ ልውውጥ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።  

የኢንተር አፍሪካ ኮፊ  ኦርጋናይዜሽን ዋና ጸሃፊ  አምባሳደር  ሶሎሞን ሩቴጋ በበኩላቸው  የአፍሪካ ቡና ኢንዱስትሪ  በበርካታ  ፈተናዎች እያለፈ መሆኑን አንስተዋል። 

የቡና ምርት ላይ እሴት አለመጨመር፣  የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ቡናን በሚፈለገው ደረጃ ያለማምረት ችግሮች ከፈተናዎች  መካከል  መሆናቸውን ጠቅሰዋል።  

በቡናው ኢንዱስትሪ መስክ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት  አህጉራዊ  ቅንጅቶች ሊጠናከሩ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም