የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአግሪኮላ ሽልማት ተምሳሌታዊ የአመራር ሰጭነት ውጤት ነው - በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአግሪኮላ ሽልማት ተምሳሌታዊ የአመራር ሰጭነት ውጤት ነው - በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በምግብ ዋስትናና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራርና ቁርጠኝነት የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት(ፋኦ) ያበረከተላቸው የአግሪኮላ ሽልማት ተምሳሌታዊ የአመራር ሰጭነት ውጤት መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ በጣሊያን ሮም የዓለም የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) የከበረውን የአግሪኮላ ሽልማትን መቀዳጀታቸው ይታወቃል።
የአግሪኮላ ሽልማት የተሰጣቸው ፈተናዎችን በመቋቋም በምግብ ዋስትና፣ በተመጣጠነ ምግብ እና በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል ባላቸው ራዕይ፣ ባሳዩት የአመራር ቁርጠኝነት እና ባመጡት ፈጣን ለውጥ ነው።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ ሺን ቺንሚን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግብርና ልማት አስተዋጽዋቸው ከፋኦ የተበረከተላቸው ሽልማት የተምሳሌታዊ አመራር ሰጭነት ውጤት ነው።
የቻይና መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአግሪኮላ ሽልማት የተሰማውን ደስታ ገልጸው፥ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ግብርናውን ለማሸጋገር ያለው ቁርጠኝነት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ምንም ጥርጥር የለውም ነው ያሉት።
በዚህም ኢትዮጵያ ከምግብ ዋስትና ችግር በመላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በኩራት ከፍ እንደምትልም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያመጣው ስኬት እንደሆነ ገልጸው፣ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ የኢትዮ-ቻይናን ጠንካራ ትብብርን ይበልጥ በማጎልበት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚያስችልም ነው ያነሱት።
ብሪክስ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ድምፅ መሆኑን ያነሱት ሺን ቺንሚን፥ ኢትዮጵያና ቻይና በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ለሚያደርጉት ትብብርም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።