የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጀግኖች ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ለከፈሉት መስዋትነት ትልቅ ክብር የሰጠ ዘመን ተሻጋሪ ሃብት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጀግኖች ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ለከፈሉት መስዋትነት ትልቅ ክብር የሰጠ ዘመን ተሻጋሪ ሃብት ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጀግኖች ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ለከፈሉት መስዋትነት ትልቅ ክብር የሰጠ ዘመን ተሻጋሪ ታሪካዊ ቅርስና የሀገር ሃብት መሆኑ ተገለጸ።
የአድዋን ድል በሚመጥንና ታሪኩን በሚያስታውስ መልኩ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታው ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ ይጠበቃል።
የድል መታሰቢያውን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና የውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ኖጎ፤ አድዋ ከሀገር ባለፈ በመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የሚኮሩበት አስደናቂ ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህንን ታላቅ ታሪክ የሚመጥን ዘመን ተሻጋሪ ሃብትና ቅርስ ገንብቶ በትውልድ ቅብብሎሽ ታሪኩ እንዲሸጋገር ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።
አድዋ አፍሪካን ለመቀራመት ቅኝ ገዥዎች እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ኢትዮጵያ የራሷንም የሌሎች አፍሪካዊያንን ነፃነት ለማስከበር ከፍተኛ መስዋእትነት የፈጸመችበት የታሪክ ምእራፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።።
በዚህም ኢትዮጵያ የነፃነት አርአያ ተደርጋ የአፍሪካ አገራት ነጻነታቸውን በትግላቸው መጎናጸፍ መቻላቸውን ዶክተር ዲማ አንስተዋል።
የኢትዮጵያውያን በአንድነትና በትብብር ለነፃነታቸው መታገል ለድል መጎናፀፍ የአድዋ ድል የመላ አፍሪካ የድል ብስራት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ለዚህ ድል መታሰቢያ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ደረጃውን በሚመጥን መልኩ መገንባቱ የሚያስደስትና የሚያስደንቅ ነው ብለዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ የቀደሙት አያቶች ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት የከፈሉትን መስዋትነት ትውልዱ በአግባቡ እንዲረዳ የሚያደርግ ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ ቅርስና የሀገር ሃብት መሆኑንም ገልጸዋል።
አድዋ ኢትዮጵያውያን በጋራ፣ በህብረትና በአንድነት ጠላትን ድል ያደረጉበት የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ደማቅ ታሪክ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የቀድሞው የጦር ሰራዊት አባል ብርጋዴር ጀነራል ካሳየ ጨመዳ ናቸው።
በመሆኑም ለአፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት ለሆነው የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ ታሪክ የሰሩትን በማክበር ትውልዱ በቀጣይ ሌላ ታሪክ እንዲሰራ ያግዛል ብለዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት፣ ታሪካዊ ዳራ እና የአድዋን መልክዓ ምድር በሚገልፅ መልኩ የተገነባ ነው።
የአድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮችን፣ የአድዋ ፈረሰኞች ማስታወሻ፣ ለሴት ጀግኖች ክብር የተሰየመ ማስታወሻ፣ የአንድነት ማዕከል፣ የአፍሪካ ነፃነት ማስታወሻ እንዲሁም የጀግኖችን ጉዞ የሚያሳዩ ድንቅ የታሪክ አሻራዎችን በውስጡ ይዟል።