ቀጥታ፡

የልማት ባንክ የስድስት ወራት አፈጻጸም ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ነው - የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት አፈጻጸም ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የባንኩ የስድስት ወራት አፈጻጸም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

በዚሁ ወቅት የባንኩ አሰራር በየጊዜው እየተሻሻለ ከመምጣቱ ባሻገር የፋይናንስ ቁመናው ጤናማ መሆኑን  አቶ አህመድ ሽዴ ገልፀዋል፡፡

በተለይም በግብርናው ዘርፍ በበጀት አመቱ ከፍተኛ ውጤት የመጣበት መሆኑ የሚበረታታ ነው ያሉት ሚኒስትሩ በቀጣይም በሁሉም ዘርፎች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ ያሉትን አማራጮች በሙሉ መጠቀምና የባንኩን የሀብት ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ባንኩ እየሰራበት የሚገኘው የብድር አሰባሰብ ስርዓት ዘላቂ እንዲሆን ለማስቻል ልምዱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ባንኩ በአምስት ዓመቱ  የስትራቴጅክ እቅዱ ያስቀመጣቸውን ዋና ዋና ስራዎችን በመለየት መፈጸም መቻሉ ለስኬት እንዳበቃው ተናግረዋል፡፡

የብድር ስርጭቱ ከዕቅድ በላይ መሆኑን ያነሱት የባንኩ ፕሬዝዳንት አፈፃፀሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ማስመዝገቡን ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይም የስትራቴጅክ እቅዱ የመጨረሻ ምዕራፍ ትግበራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የመጭው 5 ዓመት አዲስ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ ከልማት ባንክ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም