የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራዎች ለማገዝ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራዎች ለማገዝ ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል - አቶ ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ፤ ጥር 29/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራዎች በማገዝ ረገድ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አፍሪካ ድምጿን የምታሰማበት የራሷ ሚዲያ እንደሚያስፈልጋት በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ጭምር መግለጻቸው ይታወቃል።
በዚህ ረገድ ደግሞ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ራሳቸውን ማብቃትና ማዘጋጀት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘመናዊ የሚዲያ ኮምፕሌክስ አስገንብቶ በቅርቡ አስመርቋል።
የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ ያሟላ ሲሆን ሦስት የቴሌቪዥንና አራት የሬዲዮ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች አሉት።
ይህም የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ዘመናዊውን የኢዜአ ሚዲያ ኮፕሌክስ በጎበኙበት ውቅት ተቋሙ አንጋፋነቱን በሚመጥን መልኩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደራጀቱ በዘርፉ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
የዲፕሎማሲ ስራ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ብቻ የሚከናወን አለመሆኑን አንስተው፤ ኢዜአ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአዲስ ምዕራፍ የጀመረው ጉዞ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ለማገዝ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተለይ ተቋሙ የኢትዮጵያን ጥቅም መሰረት ባደረገ መልኩ በተለያዩ የዓለም አገራት ቅርንጫፎቹን ለማስፋት የያዘው ውጥን እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ኢዜአ በዓለም አቀፉ አውድ ውስጥ የኢትዮጵያን እውነት በማስተዋወቅ ረገድ የአገር ወኪልነት ሚና እንዲኖረው እንደሚያደርግም ነው ያብራሩት፡፡
በመሆኑም በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሚሲዮኖችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ ተቋማት ኢዜአ የያዘው እቅድ እንዲሳካ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡