ቀጥታ፡

የኢንሹራንስ ተቋማት አሰራራቸውን በማዘመን አካታችና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ የኢንሹራንስ ተቋማት አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ በማዘመን አካታችና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ተገለፀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ ኤፍኤስዲ አፍሪካና ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ በመተባባር የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሰራርን ማዘመን ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት አካሂደዋል።

በአውደ ጥናቱ የኢንሹራንስ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውንና አሰራሮቻቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምክረ ሀሳብ ያየዙ ፅሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ተቋማቱ የሚሰጡትን አገልግሎትና ፖሊሲያቸውን ለደንበኞቻቸው በቀላሉ የሚያስተዋውቁበት የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራም በአውደ ጥናቱ ለዕይታ ቀርቧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር በላይ ቱሉ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባንኩ የኢንሹራንስ ተቋማት ለደንበኞቻቸው የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍና ክትትል እያደረገ ነው።

ተቋማቱ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለደንበኞቻቸው የተሻለ የመድን ዋስትና አገልግሎት መስጠትና በዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችም ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ለዚህም ባንኩ የቴክኖሎጂ ባለቤቶችንና የኢንሹራንስ ተቋማት ትስስር ፈጥረው በጋራ እንዲሰሩ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት።

በኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ የፋይናንስ አካታችነት ዳይሬክተር አቤል ታደለ በበኩላቸው፥ ለዜጎች የተሻለ የመድን አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዘርፉ ጥናትና ምርምር በማካሄድ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ስራ በማስገባት ቀልጣፋና ፈጣን የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ የስልጠና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የኢንሹራንስ ተቋማት ከተለምዷዊ አሰራር በመውጣት ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት አካታች አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው አስረድተዋል።


 

በአውደ ጥናቱ የፈጠራ ስራ ካቀረቡት መካከል በኢንሹርቴክ የዳታ ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ በጋሻው፥ የኢንሹራንስ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ቀልጣፋና ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂ ማቅረቡን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም