ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲፕሎማሲ ጥረቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ወቅታዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱ ናቸው

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲፕሎማሲ ጥረቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩና ወቅታዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱ መሆናቸውን በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ገለጹ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው ከምክር ቤቱ አባላት ዲፕሎማሲን የተመለከቱ ጥያቄዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተነስቶላቸው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ያደረገና ከሀገራት ጋር ግንኙነት የምትመሰርተውም መሰረታዊ ፍላጎቶቿን ለማስከበር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ የሰጠው ለጎረቤት ሀገራት መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጎረቤቶቻችን ጋር በጋራ መልማት እንሻለን ብለዋል።

ለአብነትም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስርን በማጠናከር ኃይል የምታቀርብላቸው ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው በቅርቡም ከታንዛንያ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስምምነት ይፈረማል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ከሁሉም ጋር በትብብር ለመስራት ካላት ፍላጎት እንጂ አንዱን አቅርቦ ሌላውን ለማራቅ አይደለም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እና እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶችን በተመለከተ በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እያደረጉት ባለው ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ስኬቶች የተገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችበት የዲፕሎማሲ ጥረት ውጤትም በዘመናዊ የሀገሪቱ የዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ይወስዳል ብለዋል።

በተለዋዋጭና ተገማች ባልሆነው አለም ኢትዮጵያ ከበርካታ ሀገራት ጋር ተወዳድራ የብሪክስ አባል መሆኗ ተጽእኖ ፈጣሪነቷንና የዲፕሎማሲ ስኬታማነቷን የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲፕሎማሲ ስኬቱም በዋናነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥበብ የተሞላበት ጥረት ውጤት መሆኑን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እምርታ እያሳየ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያን ጥቅም ከማስከበር አኳያ በተለያዩ ዘርፎች ትልልቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም በስንዴ ልማት ለታየው ውጤት በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) የከበረውን አግሪኮላ ሜዳሊያ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሸለሙ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚያጎላ ነው ብለዋል።

የአለም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሁኔታ ተለዋዋጭና ተገማች ያልሆኑ ክስተቶችን እያስተናገደ ይገኛል ያሉት አምባሳደር ሽብሩ፥ በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ አመላካች ስለመሆኑም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም