በአጭር ጊዜ ትልቅ እመርታ በሌማት ትሩፋት

3201

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል የምግብ ዋስትናን ለማረጋጥ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ በምግብ እራስን ለመቻል ለሚደረገው ጥረት ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

በግብርና ልማት እየተከናወኑ ባሉ ውጤታማ ስራዎች ላይ የሌማት ትሩፋት ተግባራት ሲታከሉ ከምግብ ዋስትና ባለፈ ስርአተ ምግብን በማስተካከል ረገድ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ለመሆኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ስርአተ ምግብን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ እንዴት ይታያል? በእስካሁኑ አካሄድስ ምን ውጤቶች ተገኙ?

ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ‘የሌማት ትሩፋት’ መርሃ ግብርን ካስጀመሩ በኋላ በመህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ሌማት አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ገልጸው ነበር።

በወቅቱ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በቂ እና አመርቂ ምግብ ማግኘት መሆኑን ገልጸው በቂ የመጠን፣ አመርቂ የይዘት ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

አክለውም በምግብ ራስን መቻል ከሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ገልጸዋል።

የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር ዓላማ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥና ክብርን ማስጠበቅ ሲሆን በተለይም ስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማልማትና መጠቀምን መሰረት ያደረገ ነው።

መርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያን ደካማ የአምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን ግብ የሰነቀ መሆኑ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሌማት ትሩፋት ዘመቻው በቤተሰብ፣ ብሎም በሀገር ደረጃ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

የወተት፣ የዶሮ፣ የዕንቁላል፣ የማር፣ የዓሣ እና የሥጋ ምርቶችን ለማሻሻል ሀገራዊ የመንግሥት ፕሮግራም ሆኖ ከጥቅምት 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት በብዙ መልኩ ውጤት እያስገኘ ነው።

በእርግጥም የሌማት ትሩፋት በአንድ ዓመት ጉዞው በተለይ በወተት፣ በእንቁላል፣ በዶሮና ስጋ ምርት መጠን አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን እና ሸማቹን የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑ የተረጋገጠበት ውጤት ተመዝግቧል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በ2015 ዓ.ም፣ የወተት፣ የዶሮ እና የሥጋ ምርት መጠን በዕቅዱ መሠረት ጥሩ ውጤት ማምጣቱንና በተያዘው ዓመትም በበለጠ ለማሳካት የሁሉም ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሣ ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ጽጌረዳ ፍቃዱ በሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በማር፣ በወተትና በዶሮ ልማት ከ20 ሺህ በላይ መንደሮችን በመለየት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለአብነትም በወተት ልማት በተሰሩ ስራዎች 6 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሊትር የነበረውን የማምረት አቅም ወደ 8 ነጥብ 6 በሊዮን ሊትር ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ዓመታትም ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በእንቁላል ምርት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው የጫጩቶች ስርጭት ከነበረበት 26 ሚሊዮን ወደ 42 ሚሊዮን ማደጉን ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መርኃ- ግብር የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን የሚናገሩት የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሣ ሃብት ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ጽጌረዳ ፍቃዱ በእንስሳት ሃብት ልማት ብቻ በዓመት ለ259 ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት አመርቂ ውጤት ሳያገኝ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ዘርፉ በቅንጅት ከተመራ፣ በቴክኖሎጂ ከታገዘ  የምግብ አማራጭን ማብዛት ይቻላል።

ወተት፣ ማር፣ ስጋ እና እንቁላል መሰል የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በገበያ ላይ  ማትረፍረፍ፣ የሌማቱ በረከት ማብዛት የሚለው የብዙሃኑ እምነት ነው።

የምግብ ዋስትና ጉዳይ ከተመጣጠነ ምግብ ጋር ያለው ቁርኝት የማይነጣጠል በመሆኑ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ፋይዳው ብዙ ነው።

በሌማት ትሩፋት ገበታን በተመጣጠነ ምግብ መሙላት ከተቻለ የእናቶችንና የህጻናትን ፍላጎት በማሟላት በአካል የዳበረና በአዕምሮ የበለጸገ ትውልድ መገንባት ይቻላል።

በተቃራኒው ያልተመጣጠነ አመጋገብ ጤና ላይ ከሚፈጥረው ችግር ባለፈ በሰዎች መካከል ያለውን የኑሮ አለመመጣጠን በማስፋት፣ ማህበራዊ ቀውስን በመፈልፈልና ኢኮኖሚውን በመጉዳት ምርትና ምርታማነትን ወደ ኋላ የሚጎትት ይሆናል።

ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት በከባድ ትግል ላይ የሚገኙ ሀገራትን የልማት ግስጋሴ በመግታት ቀድሞ ወደነበሩበት የድህነት አረንቋ እንዲመለሱ ያደርጋቸዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑ ህፃናት ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዕድሜያቸው ልክ ዕድገት የማያስመዘግቡ ወይም የመቀንጨር ችግር ያለባቸው መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።

ለዚህ ነው በምግብ ራስን ከመቻል ጎን ለጎን የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ የሚሆነው።

በዚህ ረገድ የሌማት ትሩፋት እየተጫወተ ያለው ሚና ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም።

የተለያዩ ምግቦችን በገበታ ላይ ማካተት የሚያስችል ስልጠናን ከተግባራዊ የልማት ስራዎች ጋር ያካተተ ሲሆን አዲስ የአመጋገብ ባህልን የሚያለማምድ ነው።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ለተሰሩ ስራዎችና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ላሳዩት የአመራር ቁርጠኝነት በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት የከበረውን የፋኦ አግሪኮላ ሜዳልያ ተሸልመዋል። 

ሽልማቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምግብ ዋስትና እና በተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት ላሳዩት ርዕይ፣ አመራር እና ቁርጠኝነት፣ ብሎም ፈጣን፣ ተለዋዋጭ እና ፈታኝ በሆነው ከባቢያዊ ሁኔታ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተከተሉት ፈጠራዊ መፍትሔ ዕውቅና ለመስጠት የተበረከተ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ረሀብን ዜሮ ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን እንደምታደርግ ገልጸዋል። 

ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተሰሩት ስራዎች ለመጪው ትውልድ ጥሩ መሰረት የሚጥሉ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያን ለአብነት አንስተዋል።

የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ጉዟችንን በፅናት እናስቀጥላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ስራችን የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ እንሰራለን ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የኢኮኖሚ ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ነጻ አገር እውን ማድረግን ያለመ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አመራሩ ይህንን ተገንዝቦ እንዲሰራ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ህልም የሚመስሉ በርካታ አገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ የቻለችው በዜጎቿ የተባበረ ክንድ መሆኑ እሙን ነው።

ከዚህ አኳያ በምግብ ራስን ከመቻል በላይ የኢትዮጵያን የአምራችነት ታሪክ የመቀየር ግብ ለሰነቀው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መስራት ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም