ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል  የጤና መድህን አገልግሎትን ለማስፋት ለሚሰራው ሥራ ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

ጋምቤላ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎትን ለማስፋት ለሚደረገው ጥረት ያልተቆጠበ ድጋፍ እንደሚያደረግ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ። 

አገልግሎቱ ከጋምቤላ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አተገባበር ላይ ያተኮረ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል። 

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን የጤና ሽፋን ከፍ ለማድረግ በገባችው ቃል ኪዳን መሠረት በጤናው ዘርፍ የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሻሻል እየተሰራ ነው። 

በተለይ ባለፉት ዓመታት ሀገር በቀል የገንዘብ አቅምን በማስፋፋት የጤና አገልግሎቱ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሳይቆራረጥ ለህዝቡ ተደራሽ እንዲሆን በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ነው የገለጹት።    

በዚህም እንደ አገር ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ ከ55 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

በጋምቤላ ክልል በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አተገባበር ላይ መልካም ጅምሮች እንዳሉ ጠቅሰው፣ የመድረኩ ዋና ዓላማም ይህንን ለማገዝና ለማጠናከር መሆኑን ተናግረዋል።


 የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮት ጋትዊች በእዚሁ ጊዜ እንዳሉት እንደ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ ጤናማና በዓዕምሮ የዳበረ ዜጋን ማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም መንግስት ህብረተሰቡን ካልተጠበቀ ጫና ለመታደግና ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትን ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ሲያደረግ መቆየቱን አስረድተዋል። 

አቶ ሮት እንዳሉት መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በማቀፍ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። 

በዚህም በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በ10 ወረዳዎች የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመው፣ በቅርቡም ሦስት ተጨማሪ ወረዳዎችን የአገልገሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የክልሉ ጤና መድህን የቦርድ አባላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም