ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚረዳ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

ፕሮጀክቱ “ኢኔብል” የተሰኘ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኖርዌይ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የሚተገብሩት ነው።   

ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ 4 ሚሊየን ዶላር በጀት ተይዞለታል። 

በፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ፣  በአዳማ፣ በሐረርና በጅማ ከተሞች ባሉ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዙ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ነው የተገለጸው። 

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ    እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭትና ተጋላጭነትን ለመቀነስና በተለይ በነፍሰጡር እናቶችና በህፃናት ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አብራርተዋል። 

ፕሮጀክቱ በጥናትና ምርምር ላይ ተመስርቶ የሚተገበር መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ጌታቸው፤ የሕብረተሰብ ጤና ኢፒዲሞሎጂ፣ ባዮስታትስቲክስ እንዲሁም የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ላይ በጥልቀት ጥናት እንደሚያደርግ ተናግረዋል።   

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የዜጎችን ምርታማነት የሚገድብ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ሥር የሰደዱ ተላላፊ በሽታዎች ቅነሳ እንዲሁም ምርታማነት እንዲያድግ በማድረግ በኩል አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።     

የ"ኢኔብል" ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ኢሌኒ ፓፓዶፓሉ በበኩላቸው፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ላይ ሲሰራ አብዛኛውን ጊዜ በእድሜ የገፉ ሰዎች ላይ ብቻ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውሰው፤  የበሽታዎቹ ሥርጭት ወጣቶችና ህፃናት ላይ በስፋት እየተከሰተ እንደሚገኝ በምርምር መረጋገጡን አመልክተዋል።  
 

የበሽታዎቹን ሥርጭት ለመከላከል ህፃናት ከመወለዳቸው በፊት እንዲሁም በጨቅላ እድሜያቸው ላይ እያሉ የበሽታ መከላከል ሥራ በመሥራት በወደፊት እድሜያቸው ሊያጋጥም የሚችልን ተላላፊ ያልሆነ በሽታ ተጋላጭነት መቀነስ እንደሚቻልም አክለዋል።    

”ኢኔብል” ፕሮጀክት በተለይ ነፍሰጡር እናቶችና ጽንሳቸው በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ማድረግ እንዲሁም በምግብ እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ለተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንዳይጋለጡ ማድረግ በፕሮጀክቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይገኙበታል ብለዋል።  

ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ ለነፍሰጡር እናቶች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና ክትትል እንደሚደረግም ገልፀዋል።   

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም