ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ልምዷን የምታጋራባቸው የውይይት መድረኮች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ከአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ልምዷን የምታጋራባቸው የውይይት መድረኮች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ ከ37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ ልምዷን የምታጋራባቸው የውይይት መድረኮች በመሪዎች ደረጃ የሚካሄዱ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ ዝግጅት ብሔራዊ ኮሚቴ ገለጸ።
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ "ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ሥርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣ የሕይወት ዘመን፣ ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት" በሚል መሪ ኃሳብ ይካሄዳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ፤ 37ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎችና የሥራ አስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ 21 በፕሬዝዳንቶች የሚመሩትን ጨምሮ ከ30 በላይ አባል አገራት የሚሳተፉ ይሆናሉ ብለዋል።
በቀጣይ ቀናትም የሚያሳውቁ ተሳታፊ አገራት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ለጉባዔው መሳካት ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን ሥራ ማጠናቀቋን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዋ ስኬት ያስመዘገበችበት ዓመት መሆኑን አንስተዋል።
በተለይም የብሪክስ አባል መሆኗ፣ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት እውቅና መሰጠቱ ከሚጠቀሱት ስኬቶች መካከል ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም በአዲስ አበባ በሚካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ጉዳይ ላይ ትኩረት ታደርጋለች ብለዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር አየለ ሊሬ፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ በትምህርት፣ ፀጥታና ሰላም ጉዳይ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚመክር መሆኑን ጠቁመዋል።
ከሕብረቱ የመሪዎች ጉባዔ በተጓዳኝ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥና ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ እያከናወነች ያለውን ሰፊ ልምድና ተሞክሮ በመሪዎች ደረጃ በሚካሄድ መድረክ ለሌሎች የምታጋራ ይሆናል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ልማትን ማሳለጥና በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ሌላኛው ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የጎንዮሽ ስብሰባ መሆኑንም ገልፀዋል።
የአፍሪካ ሕብረት 37ኛው የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 9 እና 10 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ 44ኛው የአባል ሀገራቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ደግሞ ከመሪዎች ጉባዔ ቀደም ብሎ የካቲት 6 እና 7 ቀን 2016 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።