ቀጥታ፡

ባለፉት ስድስት ወራት ከ740 ሺህ በላይ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ከ740 ሺህ በላይ ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ  ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ከክልሎች ጋር በጋራ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በዚሁ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ፤  ሚኒስቴሩ የንፁህ መጠጥ ውሃ  ለዜጎች ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

አማራጭ የኃይል አቅርቦት፣ ከማገዶ ቆጣቢ እንዲሁም በጭስ ምክንያት በሰው ጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኃይል አቅርቦት ረገድም ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነና በጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል የታዳሽ ኃይል አቅርቦት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኃይል ዘርፉም በየዓመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ዜጎች  አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልፀዋል።


 

የሚኒስቴሩን የስድስት ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አለሙ መንገሻ፤ ባለፉት ስድስት ወራት 670 ሺህ ዜጎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ከ740 ሺህ ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከአማራጭ ኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘም 3 ሺህ 21 የባዮጋዝ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ መሆኑን ገልፀዋል።

በአጠቃላይ  በተቋሙ ዕቅድ መሠረት ከ80 በመቶ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት 67 በመቶ በላይ ሲሆን፤ በዓመቱ መጨረሻም ወደ 69 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም