ቀጥታ፡

በኢንተርፕራይዞች ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ባለፉት ስድስት ወራት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ውጭ ሀገራት ከተላኩ ምርቶች ከ17 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ።  

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የተያዘውን በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት አፈጻጸምን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህ ወቅት የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልፈታ የሱፍ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ኢንተርፕራይዞች ወደ ውጭ ሀገር ከሚልኳቸው ምርቶች ከ18 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ከ17 ሚሊየን  ዶላር በላይ ማግኘት ተችሏል።

የተገኘው ገቢ ከጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ ከአግሮፕሮሰሲንግ ምርቶችና የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ለአምራች ኢንዱስትሪዎች 2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብድር ለማቅረብ ታቅዶ 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል።

በግማሽ ዓመቱ ከ1 ሺህ 493  አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋምና ለ75 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች  የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አስረድተዋል።

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ካቀዳቸው ከ80 በመቶ በላይ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት ኤግዚቢሽንና ባዛር እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተሰሩ ሥራዎች አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን ገልፀዋል።

ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን የግብዓት ችግር ለመፍታትም በመካከላቸው የግብዓት ትስስር የመፍጠርና ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ አገራት እንዲያስገቡ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸውን የመሥሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት እያስቻለ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን አመላክተዋል።

አብዛኛዎቹ ኢንተርፕራይዞች በተቀመጠላቸው የብድር መመለሻ ጊዜ ብድራቸውን እየመለሱ መሆኑን አንስተው፤ በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ኢንተርፕራይዞች 700 ሚሊየን ብር እንዲቆጥቡ መደረጉንም ገልፀዋል።

 

 

   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም