መንግስት በድርቅ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት በድርቅ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ ይቀጥላል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ መንግስት በድርቅ ምክንያት የአንድም ሰው ህይወት እንዳያልፍ እስካሁን 11 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ከ100 ዓመታት በፊት በየ10 ዓመቱ ድርቅ ይከሰት እንደነበር ጠቅሰዋል።
በ1977 ዓ.ም በተከሰተው ድርቅም ከ750ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ደረጃው ይለያይ እንጂ ባለፉት 30 ዓመታትም በየዓመቱ ድርቅ ስለመከሰቱ አንስተዋል።
የድርቅ መኖርና የሰው በርሃብ መሞት የሚለያዩ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስት ከለውጡ ወዲህ በተፈጥሯዊ መንገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቋቋም ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ማተኮሩን ገልጸዋል።
ዘንድሮም በትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና በምስራቅ አካባቢዎች ድርቅ መኖሩን ጠቅሰው ድርቁን ለፖለቲካ አላማ ማዋል ተገቢ አይደለም ብለዋል።
ከዚህ ይልቅ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰው ህይወት እንዳያልፍ መረባረብ እንደሚገባ አንስተዋል።
ባለፉት 5 ወራት በትግራይ ክልል 500 ሺህ ኩንታል እህል በዋናነት በመንግስትና በተወሰነ ደረጃ በአጋር አካላት ለድርቅ ተጋላጭ ወደሆኑ አካባቢዎች መላኩንና ሰው በርሃብ እንዳይጎዳ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለድርቁ ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን ገልጸው ለሰብዓዊ እርዳታ ከዋለው 15 ቢሊዮን ብር ውስጥ 11 ነጥብ 4 ቢሊዮኑን መሸፈኑን ለአብነት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን በርሃብ ህይወቱ ያለፈ አንድም ሰው የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቁን ተከትሎ የሚመጡ በሽታዎች ግን የሰዎችን ህይወት ሊነጥቁ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ተመርቶ የማያውቅ ሰፊ ምርት መኖሩን ጠቅሰው በበጋ መስኖ ብቻ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መታረሱን ተናግረዋል።
ከዚህም ከ120 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይጠበቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም መንግስት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በድርቅና ሌሎች አደጋዎች የሰው ህይወት እንዳያልፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
ሆኖም ይህ የማይዋጥላቸው አካላት የስንዴ ምርታማነትንና አደጋዎችን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመሩ ስራዎችን እያጣጣሉና ድርቁን ለፖለቲካ ዓላማ ለመጠቀም እየሞከሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሚያመርተው ያለፈ ችግር ካጋጠመው ፕሮጀክት አጥፎም ቢሆን ህዝብ በርሃብ እንዳይሞት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ወቅት አንድም ሰው በድርቅ እንዳይሞት የማድረግ ሀገራዊ አቅም መኖሩን ጠቅሰው ለችግሩ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት መረባረብ የግድ ይላል ብለዋል።