የአፈር ማዳበሪያ - የምርትና ምርታማነት ሞተር - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ማዳበሪያ - የምርትና ምርታማነት ሞተር
የአፈር ማዳበሪያ የምርታማነት ሞተር ቢሆንም ቀደም ባሉት ዓመታት በግዥ የዘገየ በስርጭትም በችግሮች የተተበተበ ነበር።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማቱን የ2016 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸምና የ2016 በጀት ዓመት እቅድ በገመገመበት ወቅት የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት የአሰራር ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቦ ነበር።
የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በሩብ ዓመቱ ለግብርና ስራው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ በርካታ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውንና ከነእዚህም አንዱ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማቅረብ መሆኑን ገልጸው ነበር።
በ2015/16 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ በሕገ-ወጥ መንገድ በተሰማሩ ግለሰቦች ምክንያት እጥረት በማጋጠሙ በአርሶ አደሮች ላይ መስተጓጎል ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው ችግሩ በድጋሚ እንዳይፈጠር የአሰራር ስርዓቱን ዘመናዊ የማድረግ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በ2016/17 የምርት ዘመን 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ገልጸው በጥቅምት ወር መጨረሻ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ በማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ ተናግረው ነበር።
ቃል በተግባር
መንግስት በአጭር ጊዜ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረትና ምላሽ ሰጠ። በግብርና እና በትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴሮች በሚመራው የአፈር ማዳበሪያ ግዥና ማጓጓዝ ዐቢይ ኮሚቴ በኩል ፈጣን ተግባራዊ ርምጃ ወሰደ።
ጥቅምት 22 ቀን 2016 የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በጅቡቲ ኦልድ ፖርት (ኤስ.ዲ.ቴቪ ወደብ) ተገኝተው የ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን በይፋ አበሰሩ።
አቶ አደም ፋራህ በወቅቱ ለ2016/2017 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንና የአፈር ማዳበሪያ ግዥና የአስተዳደር ሥርዓቱ እንዲሻሻል መደረጉን ተናግረዋል።
የወጭ ንግድ አቅምን የሚያሳድጉ እንደ ስንዴ፣ አቦካዶ፣ ቡናና ሻይ ያሉ ምርቶችን በስፋት ማምረት የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀደም ብሎ መፈጸሙም ማዳበሪያን በወቅቱ ለማድረስ፣ የማጓጓዝ ስራ ላይ መስተጓጎል እንዳይፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን የሚውል የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከግዥ ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ ባለው ሂደት ጠንካራ ስራ እየተከናወነ መሆኑን በመጥቀስ ለምርት ዘመኑ 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ካለፈው ዓመት የምርት ዘመን ጋር ሲነፃጸርም በ2016/17 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በብዛት፣ በአነስተኛ ዋጋ እና በጥራት መግዛት እንደተቻለ ጠቅሰው የግብርና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ፍላጎትን ለመሙላት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በ2015/16 በጀት ዓመት ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን አስታውሰው በዘንድሮው የ2016/17 የምርት ዘመንም ከ23 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያው በጊዜ ማስገባት መቻሉም ቀድመው ለሚዘሩ አካባቢዎች፣ ለበጋና መኸር ወቅት ሰብል ልማት ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫዎት ተናግረዋል።
ወቅትን ብቻ ተከትሎ የሚገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ዓመቱን ሙሉ የመደበኛውን የወጪና የገቢ የሎጀስቲክ አገልግሎት ሳያስተጓጉል እንዲገባ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ከመደበኛ ወጪና ገቢ የሎጀስቲክስ አገልግሎት ጎን ለጎን የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዝ ሂደትን ለማሳለጥ ዓላማ ያደረገ ስራ መሰራቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭት አሰራር ላይ መንግስት ማሻሻያ ማድረጉን ተከትሎ የአሰራር ሂደቱን የሚመራና የሚከታተል ቦርድ ተዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ወቅቱን ባለመጠበቁ የመደበኛ ሎጀስቲክስ አገልግሎቱን ሲጎዳ ቆይቷል፤ በተያዘው ምርት ዘመን መሰል ጫና እንዳይከሰት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በተለይ ወቅትን ብቻ ተከትሎ የሚገዛውን የአፈር ማዳበሪያ ዓመቱን ሙሉ የመደበኛውን የሎጀስቲክ አገልግሎት ሳያስተጓጉል እንዲገባ ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት መደረሱን ተናግረዋል።
ውጤት
በዚህም እስከ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም ለዘንድሮ መስኖ ልማት የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን የአፈር ማዳበሪያ ግዥና ማጓጓዝ ዐብይ ኮሚቴ አስታውቋል።
በምርት ዘመኑ ከሚያስፈልገው ማዳበሪያ 25 በመቶው ለመስኖ፣ 20 በመቶ ለበልግ እና 55 በመቶ ለመኸር እርሻ በማከፋፈል ግዥ መፈጸሙን ለመስኖ ስራዎች የሚውል የአፈር ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ጠቅሷል።
ለዘንድሮ ምርት ዘመን የሚያስፈልገው ማዳበሪያ አብዛኛው ግዥ መፈጸሙንና ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑን የገለጸው ዐቢይ ኮሚቴው ሎጂስቲክሱን ለማሳለጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ መሆኑንም ገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል የአፈር ማዳበሪያ ግዥና ስርጭትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቀደሙት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ በትኩረት በመሰራቱ ውጤት እየተገኘ መሆኑን በማብራሪያቸው አንስተዋል።
አምና የግዥ መዘግየትም የስርጭትም ችግር እንደነበር አስታውሰው በተወሰደው የመፍትሄ ርምጃ የአፈር ማዳበሪያን ቀድሞ በመግዛት ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣይ ትኩረት
የምርትና ምርታማነት ሞተር ለሆነው የአፈር ማዳበሪያ በተሰጠው ልዩ ትኩረት የግዥና የማጓጓዝ ስራዎች በተሳካ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው።
ትልቁ ግብ ግን ለአርሶ አደሩ በጊዜ እንዲደርስ በማድረግ ጥቅም ላይ መዋሉን ማረጋገጥ መሆኑ እሙን ነው።
ከዚህ አኳያ በእስካሁኑ ሂደት የተለያዩ ክልሎች የግብርና ቢሮዎች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ከተደራሽነት አኳያም በትኩረትና በጥንቃቄ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ነገር ግን በተለይ ግዙፍ መጠን ያለው የአፈር ማዳበሪያ የሚፈልገውን (በአጠቃላይ ከሚያስፈልገው 55 በመቶ ድርሻ የሚወስደውን) የመኸር እርሻ ታሳቢ ያደረገ የአፈር ማዳበሪያ ስርጭት ላይ መረባረብ ያሻል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም በስርጭት ሂደት ሊያጋጥም የሚችልን ችግር ቀድሞ መከላከል ላይ ባተኮረ መልኩ መስራት በሁሉም አካባቢዎች የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።